ከሄሊኮፕተር ጋር ተጋጭቶ ወንዝ ውስጥ ከገባው አውሮፕላን በህይወት የተገኘ የለም ተባለ
64 ሰዎች ካሳፈረው የአሜሪካ ኤርላይንስ አውሮፕላን መንገደኞች ውስጥ የ28ቱ አስከሬን መገኘቱ ተገልጿል
300 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ያደረጉት ርብርብ ተስፋ ወደማስቆረጡ ተቃርቧል
ከሄሊኮፕተር ጋር ተጋጭቶ ወንዝ ውስጥ ከገባው የአሜሪካ አውሮፕላን መንገደኞች የተረፈ ሰው አለመኖሩ ተነገረ።
60 መንገደኞች እና አራት የበረራ ቡድን አባላትን ያሳፈረው የአሜሪካ ኤርላይንስ አውሮፕላን በዋሽንግተን ዲሲ ሮናልድ ሬገን አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲቃረብ ከአሜሪካ ጦር ሄሊኮፕተር ጋር መጋጨቱ ይታወሳል።
የመንገደኞች አውሮፕላኑ ከግጭቱ በኋላ በፓቶማክ ባህር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ከ300 በላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በምሽትና በአስችጋሪ የአየር ሁኔታ የነፍስ አድን ስራ ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል።
የዋሽንግተን ዲሲ የእሳት አደጋ መከላከያ ተቋም ሃላፊው ጆን ዶኒ ከጥቂት ስአት በፊት በሰጡት መግለጫ የነፍስ አድን ስራው ተስፋ ወደማስቆረጡ መቃረቡን ተናግረዋል።
እስካሁን የ27 የአሜሪካ ኤርላይንስ መንገደኞችና በሄሊኮፕተሯ ከተሳፈሩ ሶስት ወታደሮች የአንዱ አስከሬን መገኘቱን አብራርተዋል።
የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሲን ዱፊ በበኩላቸው አውሮፕላኑ ወደ ባህሩ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ በሶስት የተለያየ አቅጣጫ ተቆራርጦ መገኘቱን መግለጻቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል።
የአሜሪካ ኤርላይንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሮበርት ኢሶም በሮናልድ ሬገን አውሮፕላን ማረፊያ ሊያርፍ የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን "በትክክለኛው አቅጣጫ" እየተጓዘ እንደነበር በምርመራ መረጋገጡን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም በትሩዝ ሶሻል ማህበራዊ ሚዲያቸው ባጋሩት ጽሁፍ "አውሮፕላኑ በትክክለኛ መስመሩ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እየተቃረበ ነበር፤ ሄሊኮፕተሩ ደግሞ ዘለግ ላለ ጊዜ ወደ አውሮፕላኑ በቀጥታ ሲያመራ ታይቷል" ብለዋል።
"የአውሮፕላኑ መብረት ከርቀት የሚታይ ሆኖ ሳለ ሄሊኮፕተሩ ከፍታውን ወይም አቅጣጫውን ሳይቀይር ከ አውሮፕላኑ ጋር ለምን ተጋጨ የሚለው አጠያያቂ " ነው ሲሉም አክለዋል።
የአቪየሽን ባለሙያዎች በርካታ በረራዎችን የሚያስተናግደው የሮናልድ ሬገን አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ አስቸጋሪ ከሆኑ ኤርፖርቶች መካከል አንዱ መሆኑን እየገለጹ ነው።
የአሜሪካ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር (ኤፍኤፍኤ) "ሊቀረፍ ይችል ነበር" የተባለውንና ከ60 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን የአውሮፕላን ግጭት አደጋ መንስኤ እየመረመረ ነው ተብሏል።