የህወሓት ታጣቂዎች በቆቦና አካባቢው ከ100 በላይ ዜጎችን አግተው መውሰዳቸውን ነዋሪዎች ገለጹ
የቆቦና ዝቋላ ወረዳ ነዋሪዎች ምግብና እንስሳት በህወሓት ታጣቂዎች በመዘረፋቸው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል
የአማራ ክልል መንግስት ከህወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች ላሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል
የህወሓት ታጣቂዎች በቆቦ እና አካባቢው ከ100 በላይ ዜጎችን አግተው መውሰዳቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ከነሀሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ወሎ፣ ዋግህምራ፣ በወልቃይት እና አፋር በኩል አዲስ ጥቃት መክፈቱን የፌደራል መንግስት መናገሩ ይታወሳል።
ህወሓት በበኩሉ የፌደራል መንግስት አዲስ ጥቃት እንደከፈተበት ገልጾ ጥቃቱን በመመከት ላይ መሆኑን በወቅቱ አሳውቆ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ግን የህወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ያሉ የዋግ ህምራ እና ሰሜን ወሎ ዞን ስር ያሉ የቆቦ፣ ዝቋላ እና አካባቢውን ተቆጣጥረው ቆይተዋል።
አሁን ላይ በህወሓት ቁጥጥር ስር ቆይተው የነበሩ እነዚህ አካባቢዎች ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ ህይወት ምን እንደሚመስል አል ዐይን አማርኛ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች አነጋግሯል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቆቦ ነዋሪ እንደነገሩን ከሆነ የህወሓት ታጣቂዎች ከአንድ ዓመት በፊት ቦታውን ተቆጣጥረው እንደነበር ገልጸው፤ በአሁኑ ቆይታቸው ግን ከአምናው የባሰ አስከፊ ጉዳት እንዳደረሱ ነግረውናል።
“የህወሓት ታጣቂዎች መስከረም 2 ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት ላይ የ23 ዓመት ወጣት ወንድሜን ጨምሮ ሁለት ሰዎችን ሲገድሉ ስድስት ወጣቶችን ደግሞ አቁስለዋል” ብለዋል።
ታጣቂዎቹ ንጹሃንንን የገደሉት ንብረት ለመዝረፍ ሲሞክሩ እንዲተውለት የለመኗቸውን፣ ከመንግስት ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል የጠረጠሯቸውን እንዲሁም የሚሊሻ እና ፋኖ አባል የሆኑ ቤተሰቦች አላችሁ በሚል የጠረጠሯቸውን ነውም ብለዋል።
“በአጠቃላይ የህወሓት ታጣቂዎች በቆቦ ከተማ እኔ የማውቃቸውን በአንድ ቀን ብቻ ስድስት ሰዎችን መግደሉን አውቃለሁ” ያሉን ይህ ነዋሪ በቆቦ ከተማ ፣ አርበት፣ ዞብል ተራራ እና ዙሪያው ባሉ ቀበሌዎች ውስጥ ይኖሩ ከ100 በላይ ሰዎች በህወሓት ታጣቂዎች ታፍነው እንደተወሰዱ ተናግረዋል።
በህወሓት ታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱት ዜጎች ወጣቶች፣ የጦር መሳሪያ ይኖራቸዋል እና መረጃ ይሰጣሉ በሚል የጠረጠሯቸውን እንደሆነም ነዋሪው ጠቁመዋል።
ታጣቂዎቹ ከግድያ በተጨማሪም ከነዋሪዎች ቤት የሚለበስ ነጠላ ሳይቀር ከመዝረፋቸው ባለፈ ቁጥራቸውን ለጊዜው ያልታወቁ ሴቶች እና ህጻናት በታጣቂዎቹ መደፈራቸውን ገልጸዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት በነበረው ጦርነት ወድመው የነበሩ የህዝብ መገልገያ ተቋማት በክልሉ መንግስት እና በለጋሽ ተቋማት መልሰው ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ጤና ጣቢያዎች ፣ የውሃ እና ትምህርት ተቋማት ዳግም መዘረፋቸውን እና መውደማቸውም ተገልጿል።
አሁን ላይ የህወሓት ታጣቂዎች ከነሀሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በፊት ወደ ነበሩባቸው አካባቢዎች መስፈራቸውን የነገሩን እኝህ ነዋሪ ታጣቂዎቹ ተመልሰው ሌላ ጥቃት እንዳይከፍቱባቸው ስጋት እንዳላቸውን አክለዋል።
የቆቦ ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች ያላቸው ንብረት በተለይም እህል እና ሌሎች ምግቦች በህወሓት ታጣቂዎች በመዘረፋቸው ለረሀብ መጋለጣቸውን የተናገሩት ነዋሪው መንግስት የሰብዓዊ ድጋፎችን እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
ሌላኛው በህወሓት ታጣቂዎች ስር ቆይተው የነበሩ እና አሁን ላይ ነጻ የወጡ አካባቢ በዋግ ህምራ ዞን በዝቋላ ወረዳ ስር ያሉ ቀበሌዎች ሲሆኑ፤ ንጹሃን ንብረታቸው በታጣቂዎቹ ከመዘረፉ ባለፈ የህወሀት ቁስለኞችን እንዲንከባከቡ፣ የሞቱትን እንዲቀብሩ እና ሌሎች የስነ ልቦና ጥቃቶች ሲደርስባቸው እንደቆየ ሰምተናል።
በዋግ ህምራ ዞን ካሉ ወረዳዎች ውስጥ ሁለቱ አሁንም በህወሓት ታጣቂዎች እንደተያዙ ናቸው ያሉን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጽጽቃ ከተማ አስተያየት ሰጪ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በስቃይ እንዳሳለፉ ተናግረዋል።
የሕወሃት ታጣቂዎች በቅዳሚት ማዕከል ስር የነበሩ ስድስት ቀበሌዎችን ከነሀሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ይዘዋቸው እንደነበር ነግረውን አሁን ላይ ግን እነዚህ አካባቢዎች ነጻ መውጣታቸውን አስተያየት ሰጪው ነግረውናል።
ታጣቂዎቹ በአንድ ወር ውስጥ ስንቅ ለህወሓት ከማዋጣት ጀምሮ፣ ከመንግስት ጋር ንኪኪ አላችሁ በሚል የጠረጠሯቸውን መሬታቸውን ቀምተው ነበር ያሉን ሲሆን አጠቃላይ ነዋሪው ደግሞ ለብዙ እንግልት ተዳርገን ነበርም ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት አሁንም በህወሓት ታጣቂዎች ስር ያሉ የዋግ ህምራ ወረዳዎችን ነጻ እንዲያወጣቸውም እና የምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎች እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብተው በበኩላቸው በህወሓት ወረራ ከ1ሺህ 100 በላይ የጤና ተቋማትን አውድሟል ብለዋል።
ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የወደመው የጤና መሰረተ ልማቶች የመልሶ ግንባታ ስራዎች መጀመራቸውን የገለጹት ሀላፊው ህወሓት በክልሉ ባደረገው ወረራ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚገመት የጤና መሰረተ ልማት መውደሙን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በበኩሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተጎጂዎች ድጋፎችን እያጓጓዘ እንደሆነ ገልጿል።
ከዚህ በፊት በህወሓት ታጣቂዎች ጥቃት ሰግተው ተፈናቅለው በተጠለሉባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የገለጸው ኮሚሽኑ አሁንም አካባቢዎቹ ከህወሓት ነጻ መሆናቸውን ተከትሎ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ለተመለሱ ዜጎች ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ከአማራ መልሶ ማቋቋም ድርጅት እንዲሁም ከሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ ዞኖች ጋር እየመከረ መሆኑንም አስታውቋል።
የአፍሪካ ህብረት በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል መንግሥት እና ህወሓት መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ እና ሁለቱ አካላት ወደ ድርድር እንዲገቡ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ሁለቱም አካላት ህብረቱ በደቡብ አፍሪካ እንዲካሄድ የታቀደውን ድርድር መቀበላቸውን ማሳወቃቸውም አይዘነጋም።