መንግስት የሕዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ሲባል የመከላከያ ኃይል የቆቦ ከተማን መልቀቁን አስታውቆ ነበር
ቆቦ ከተማን የተቆጣጠሩት የህወሓት ታጣቂዎች ንጹሃንን መግደላቸውን የራያ ቆቦ ወረዳ ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ገለጹ።
መንግስት የሕዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ሲባል የመከላከያ ኃይል የቆቦ ከተማን መልቀቁን መግለጹን ተከትሎ የህወሃት ታጣቂዎች በራያ ቆቦ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮችንና ወጣቶችን መገደላቸውን ነዋሪዎቹ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
ለደህንነታቸውን ሲባል ድምጻቸውን ቀንሰው በስልክ ያነጋገሩን ግለሰብ፤ በከተማዋ ወጣቶች መገደላቸውን ተናግረዋል። በቆቦ ከተማ ስልክ ይዞ መገኘት እንደሚስገድል የተናገሩት አስተያየት ሰጭዋ፤ የተገደሉ ወጣቶች አስክሬን አሁንም አለመነሳቱን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በቆቦ ከተማ በተለያዩ መንገዶች ላይ የተገደሉ ወጣቶች አስክሬን እንዳለ የተናገሩት ደግሞ ሌላ አስተያየት ሰጭ ናቸው። አሁን ባለው ሁኔታ አስክሬን ማንሳት እንዳልተቻለ የተገለጸ ሲሆን አሁንም ውጊያ እንዳለ ተናግረዋል።
ወጣቶቹ እና አርሶ አደሮቹ “ፋኖ ናችሁ፤ የብልጽግና አባል ናችሁ፤ ሚሊሻ ናችሁ” በሚል ግድያ እየተፈጸመ እንደሆነ ገልጸዋል። በሮቢት ከተማ ብቻ ሁለት ወጣቶች መገደላቸውን ከስፍራው ወደ ወልዲያ የመጣ አንድ አስተያየት ሰጭ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል።
አሁን ላይ ጦርነት እየተካሄደ ያለው በሮቢት እና ጎብዬ መካከል መሆኑም አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል። አሁንም በቆቦ ከተማ የቤት ለቤት አሰሳ እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ቤት ዘግተው መቀመጣቸውን ገልጸዋል።
የጎብዬ እና ወልዲያ ነዋሪዎች አሁን ላይ በጦርነቱ ምክንያት “ለሌላ ስደት እንዳረጋለን” የሚል ስጋት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
መንግስት የቆቦ ከተማን በመልቀቅ እና ወደ ኋላ መጥቶ ለመከላከል የሚስችለውን ወታደራዊ ይዞታዎችን ለመያዝ መገደዱን ከገለጸበት ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ እስከአሁን ከተማዋ በአማጺው ቁጥጥር ስር እንደሆነች ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት የተኩስ አቁም ካወጀ ከወረት በኋላ በኋላ አሁን ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳግም ጦርነት እየተካሄደ ነው።
የቆቦ ከተማ አስተዳደር፤ የሰሜን ወሎ ዞን ፤ የአማራ ክልል እና ለፌዴራል መንግስት የኮሙኒኬሽን ቢሮዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ አል ዐይን አማርኛ ጥያቄ ቢያቀርብም የስራ ኃላፊዎቹ ስልክ ማንሳት ባለመቻላቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ለወራት ቆሞ የነበረውን ጦርነት መጀመሩን ባወጡት ባሳለፍነው ረቡዕ ነሃሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ህወሓት ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሰራዊትና እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃይሎች ትግራይ ደቡባዊ አቅጣጫ ባለው ግንባር በኩል ተኩስ መክፈታቸውን አስታውቋል።
የህወሓት መግለጫን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በዛሬው እለት ጠዋት 11 ሰዓት በተያየ አቅጣጫ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል።
የፌደራል መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው ህወሓት ጋር ያለውን ግጭት በድርድር ለመፍታት ማስታወቁ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚደረደር መግለጹ ይታወሳል። ህወሓትም በተመሳሳይ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር።