የኒውዝላንድ ሐኪሞች የምግብ መመገቢያ ሳህን ያህል ስፋት ያለው እቃ በታካሚ ሆድ ውስጥ ረስተው ተገኙ
ለወሊድ ሕክምና ወደ ሆስፒታል ያመራችው እንስት ለ18 ወራት የተረሳ እቃ ወጥቶላታል ተብሏል
የሕክምና ስህተቱን የፈጸመው የሐኪም ቡድን ላይ እርምጃ አልተወሰደበትም መባሉ ብዙዎችን እንዳላስደሰተ ተገልጿል
የኒውዝላንድ ሐኪሞች የምግብ መመገቢያ ሳህን ያህል ስፋት ያለው እቃ በታካሚ ሆድ ውስጥ ረስተው ተገኙ፡፡
ስሟ ለደህንነቷ በሚል ያልተጠቀሰች አንድ እንስት ከወር አበባ ህመም ጋር በተያያዘ ህክምና ለመከታተል በሚል ነበር ወደ ኦክላንድ ሆስፒታል ያመራችው፡፡
እንስቷ ከህመሟ ለመፈወስ የቀዶ ጥገና ህክምና እንደሚያስፈልጋት ከተነገራት በኋላ ተስማምታ ህክምናውን ጀምራለች ተብሏል፡፡
የቀዶ ህክመናዋን አጠናቃ ወደ ቤቷ ያመራችው ይህች እንስት በተደጋጋሚ ህመም እየተሰማት ወደ ሆስፒታሉ ብትመላለስም ምንም አይነት የጤና እክል እንደሌለባት እየተነገራት ተመላልሳለች፡፡
በመጨረሻም በተደረገ ምርመራ በእንስቷ ሆድ ውስጥ የምግብ ማቅረቢያ ያህል ስፋት ያለው እቃ በሆድ እቃዋ ውስጥ መገኘቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ በእንስቷ ሆድ ውስጥ ተረስቶ የነበረው እቃ የቀዶ ጥገና ቁሳቁስ ማስቀመጫ ፕላስቲክ ሲሆን ከ18 ወራት በኋላ በሌላ ጥገና ከሆዷ ውስጥ ወጥቷል፡፡
ስህተት በተፈጠረበት የመጀመሪያው ቀዶ ጥገና ላይ የቀዶ ጥገና ሐኪምን ጨምሮ ስምንት የህክምና ቡድን አባላት ተሳትፈዋል የተባለ ሲሆን የቀዶ ጥገና ቡድን መሪው ታካሚዋን ይቅርታ መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡
በዚህ ሆስፒታል ላይ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ የሕክምና ስህተት ተፈጽሞ ነበር የተባለ ሲሆን ስህተቱን በፈጸሙ የህክምና ቡድን አባላት ላይ እርምጃ አልተወሰደም ተብሏል፡፡
የኒውዝላንድ ጤና እና አካል ጉዳተኝነት ኮሚሽነር የህክምና ስህተት በፈጸሙት ሐኪሞች ላይ እርምጃ አለመወሰዱን ተችተዋል፡፡
የሕክምና ስህተት የተፈጸመባት እንስት ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ ጠበቆችን በማካከር ላይ እንደሆነችም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡