የባከነ ደቂቃ ጭማሪ መብዛት የስፖርት ቤተሰቡን በሁለት ጎራ ከፍሎታል
የኳታሩ የአለም ዋንጫ በባከነ ስአት ጭማሪ ከወዲሁ ክብረወሰን ሊይዝ የተቃረበ ይመስላል።
እስካሁን በተደረጉ አምስት የምድብ ጨዋታዎች ብቻ 85 ደቂቃዎች ተጨምረዋል።
እንግሊዝ ኢራንን 6 ለ 2 ያሸነፈችበት ጨዋታ የተጠናቀቀው በ117 ደቂቃ ከ16 ሰከንዶች ነው።
ሳኡዲ አረቢያ በዛሬው እለት አርጀንቲናን ባሸነፈችበት ጨዋታም በመጀመሪያው አጋማሽ ሰባት ደቂቃ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ 14 ደቂቃዎች ተጨምረዋል።
በቪዲዬ የታገዘ ዳኝነት ወይም ቫር፣ የተጫዋቾች ቅያሪ እና ጉዳቶች፣ የፍፁም ቅጣት ምት እና ቀይ ካርድ ውሳኔዎች የጨዋታውን ጊዜ ያባክናሉ፤ አንዳንድ ተጫዋቾችም የጨዋታውን ፍጥነት ሆን ብለው በማጎተት ስአት ለመግደል ሲሞክሩ ይታያል።
የፊፋ የዳኞች ኮሚቴ ሊቀመንበሩ ጣሊያናዊው ፔርሉጂ ኮሊና ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ 4ኛ ዳኞች የባከነ ጊዜ ቁጥጥራቸውን ጠበቅ እንዲያደርጉ ተነግሯቸውል ብለዋል።
በሩስያው የአለም ዋንጫ የተጀመረው ጥብቅ ቁጥጥር ከ6 እስከ 8 ደቂቃ እንዲጨመር ማድረጉንም ነው ያወሱት።
ጎል የሚያስቆጥሩ ተጫዋቾች ደስታቸውን ለመግለፅ የሚያጠፉት ጊዜ ዋጋ እንዳያስከፍላቸውም ነው የቀድሞው ተወዳጅ ዳኛ ያሳሰቡት።
በሩስያ የተጀመረው የነኮሊና እርምጃ የኳታሩን የአለም ዋንጫ በተጨማሪ ስአት ክብረ ወሰን ሊያስይዘው ተቃርቧል።
አምስቱ የምድብ ፍልሚያዎች ላይ በሁለቱ አጋማሾች የተሰጡ ተጨማሪ ደቂቃዎች ከፈረንጆቹ 1966 ወዲህ ረጅም ሆነው ተመዝግበዋል።
እንግሊዝ ከኢራን በመጀመሪያው አጋማሽ 13.59 ሰከንድ
አርጀንቲና ከሳኡዲ አረቢያ በሁለተኛው አጋማሽ 13.53 ደቂቃ
እንግሊዝ ከኢራን በሁለተኛው አጋማሽ 13.05 ደቂቃ፣
አሜሪካ ከዌልስ በሁለተኛው አጋማሽ 10.32 ደቂቃ
ሴኔጋል ከኔዘርላንድስ በሁለተኛው አጋማሽ 10.03 ደቂቃ ተጨምሮ ተጠናቀዋል።
በእነዚህ ተጨማሪ ደቂቃዎች ጎሎችም ተቆጥረዋል።
ሜህዲ ታረሚ ኢራንን ከሽንፈት ባይታደግም ሁለተኛዋን የፐርሺያ ኮከቦች ጎል ያስቆጠረው 102.30 ደቂቃ ላይ ነው (ጨዋታው ከነጭማሪ ደቂቃው ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ሲቀረው)።
ዳቪ ክላሰን ለኔዘርላንድስ በ98ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎልም ከታራሚ ቀጥላ ባለቀ ስአት የተገኘች ሆናለች (2 ደቂቃ ሲቀር)።
የኳታሩ የአለም ዋንጫ በተለመደው ጊዜ ያለመጠናቀቅ የስፓርት አፍቃሪዎችን ለሁለት ከፍሏል፤ አንዳንዶች የፊፋን የባከነ ስአት ቁጥጥር ሲያደንቁ ሌሎች ደግሞ የተንቀራፈፉ ጨዋታዎች አሰልቺ እንዳይሆኑ ስጋት አላቸው። እርሶስ ምን አስተያየት አለዎት?