ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከስዊድኑ አቻቸው ስቴፋን ሎቭን ጋር ተገናኝተው ተወያዩ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከስዊዲን ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፋን ሎቭን ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽና ቀጣናዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በኖርዌይ ኦስሎ የኖቤል ሽልማታቸውን ለመቀበል ወደስካንዲኒቪያን ባቀኑበት አጋጣሚ ነው በ ስዊዲን ትናንት ህዳር 29 ጉብኝት ያደረጉት፡፡
በቆይታቸውም ሁለቱ መራሔ መንግሥታት ስለ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ፣ ስለ ቀጣናዊ መረጋጋት፣ እንዲሁም በፖለቲካዊ አመራር ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ስለማበረታታት ተወያይዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሎቨን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኖቤል ሽልማት በማግኘታቸው የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እየወሰዷቸው ስላሉት የለውጥ ርምጃዎች እና ተግባራት የስዊድን መንግሥት ያለውን አድናቆትም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው እያካሄደ በሚገኘው ቀጣይነት ያለው የለውጥ ጉዞ ወቅት ስለሚያጋጥሙ ሳንካዎች አንስተው፣ ከጨለማ አስተሳሰብ ይልቅ ነገን የተሻለ የማድረግ እምነት በመያዝ ይሄው እውን እንዲሆን መትጋት እንደሚገባ በማንሳት ከስዊኑ አቻቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡
ከስዊዲን ቆይታቸው በኋላ የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ኖርዌይ በማቅናት በኦስሎ ከኖቤል ኮሚቴ አባላት ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማታቸውን ዛሬ ይቀበላሉ፡፡
መረጃውን ያገኘነው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ማህበራዊ ገጽ ነው፡፡