ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመከላከያ ሚኒስትርን ጨምሮ 10 ሹመቶችን ሰጥተዋል
በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ማን በማን ተተካ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተለያዩ ሹመቶችን መስጠታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል። የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በትናንትናው እለት ስብሰባ አድርጎ የተለያዩ ዉሳኔዎችን ካሳለፈ በኋላ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን ሹመታቸውን ይፋ ያደረጉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ አስር ሹመቶችን የሰጡ ሲሆን በቅርቡ ከብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት በታገዱት አቶ ለማ መገርሳ ቦታ ዶ/ር ቀንዓ ያደታ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፡፡
አቶ ለማ መገርሳ በስራ ቦታቸው ላይ እንዲሁም በፓርቲው ስብሰባዎች እንደማይገኙ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው መታገዳቸውን ተከትሎ ፓርቲው መግለጹ ይታወቃል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሸሙት ዶ/ር ቀንዓ ያደታ የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አባል ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሰላም እና ደህንነት (Peace and Security) ፒኤችዲ ያላቸው ዶ/ር ቀንዓ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሹመት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡ ካገለገሉባቸው ኃላፊነቶች መካከል የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ፣ የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ፣ የኦሮምያ አስተዳደር ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ፣ የጅማ ዞን ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፣ የጉምሩክ ኃላፊ እና የሰንዳፋ ፖ/ኮሌጅ ዲን ሆነው ያገለገሉበት ይገኙበታል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከኃላፊነታቸው ተነስተው በምትካቸው ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ተሾመዋል፡፡ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነበሩ፡፡
የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ በፕሮፌሰር ኂሩት ወልደ ማርያም ምትክ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሆነዋል፡፡ በእርሳቸው ቦታ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ኢንጂነር ታከለ ኡማ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሾመዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ዳባ እና አቶ ፍቃዱ ጸጋ ደግሞ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሹመት ሰጥተዋቸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጣቸውን ሹመት አልቀበልም በማለት ተንሳፈው የቆዩት አቶ ዮሐንስ ቧያለው አሁን የኢትዮጵያ የውጭ ግነኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ አዲስ ሹመት ተሰጥቷቸዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ ቧያለው በሕይወት በሌሉት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም የተሰየመን ተቋም የማገልገል ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ የቀድሞውን ሹመት ላለመቀበላቸው ምክንያት መሆኑን በወቅቱ ለአል ዐይን ገልጸው ነበር፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የነበሩት አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ዛሬ አዲስ ሹመት አግኝተዋል፡፡
አቶ እንደአወቅ አብቴ ከአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባነታቸው ተነስተው የብረታ ብረት ኢንጅኔሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ፕሮፌሰር ኂሩት ወልደ ማርያም በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ፕሮፌሰር ኂሩት በቅርቡ ከአቶ ለማ መገርሳ እና ዶ/ር ሚልኬሳ ሚደጋ ጋር ከብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የታገዱትን የወ/ር ጠይባ ሀሰንን ቦታ ነው የተኩት፡፡
በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ሹመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቦ ሲጸድቅ የሚጸና ይሆናል፡፡