የለማ መገርሳን ከአባልነት መነሳት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባበለ
ከአባልነት ተነስተዋል የተባሉት ወ/ሮ ጠይባ ሀሠንም ሆኑ ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) ቀድሞውኑ የምክርቤቱ አባል እንዳልነበሩም ገልጿል
ምክር ቤቱ “አቶ ለማ አሁንም አባል እንደሆኑና በዚሁ እንደቀጠሉ ነው የማውቀው” ሲል ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቋል
የለማ መገርሳን ከአባልነት መነሳት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባበለ
የኦሮሞ ህዝብን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የሆኑ ሶስት የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ከአባልነት ተነስተዋል መባሉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባበለ።
የባለስልጣናቱን ከአባልነት መነሳት በተመለከተ በይፋ የደረሰኝ ደብዳቤም ሆነ ሌላ ነገር የለም ያለው ምክር ቤቱ ለጊዜው የተነሳ ነገር እንደሌለ አስታውቋል።
"ተነሱ የሚለው ወሬ ከየት እንደተገኘ ራሱ አናውቅም" ያሉት የምክርቤቱ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ካሳሁን በቀለ "አዲስ የመጣም ሆነ የተነሳ ሰው የለም" ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ጠይባ ሀሠንም ሆኑ ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) ቀድሞውኑ የምክርቤቱ አባል አልነበሩም ያሉት አቶ ካሳሁን የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ የምክር ቤቱ አባል እንደሆኑና አሁንም በዛው እንደቀጠሉ ነው የምናውቀው ብለዋል።
በእነ አቶ ለማ ቦታ ተተኩ የተባሉትን ሶስት የክልሉን የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የአመራር አባላት በተመለከተ አል ዐይን ላቀረበላቸው ጥያቄም ባለሙያው "አቶ ፍቃዱ እና አቶ ሳዳት በፊትም የምክር ቤቱ አባል ናቸው" ሲሉ መልሰዋል።
አቶ ፈቃዱ ተሰማ የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣ አቶ ሳዳት ነሻ ደግሞ የጽህፈት ቤቱ የከተማ ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ናቸው።
የመከላከያ ሚኒስትሩን አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ የነበሩት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰንና የኦሮሚያ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ታግደዋል መባሉ የሚታወስ ነው።