ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ‘ሀገሪቱ ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ እያመራች ነው’ መባሉን ውድቅ አደረጉ
ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያ የሰላም እጦት ምንጩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነው ሲሉ ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሀገሪቱ በፈተና ውስጥ ሆናም እያደገች ነው ሲሉ የመንግታቸውን ስራ አወድሰዋል
የህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት ባካሄደው 28ተኛ መደበኛ ጉባኤ ከም/ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሰላምና ደህንነት ስጋቶች ጎልተው በተጠየቁበት የፓርላማ ውሎ፤ በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልል ያለው የደህንነት ስጋቶች ተጠይቀዋል።
የሀገሪቱ የሰላም እጦትና "የመንግስት አቅም" ጥያቄ በተነሳበት የፓርላማ ውሎ፤ አዲሱን የ2016 ዓመት ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠመንጃ ዝቅ እንዲልና ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ወደ ሰላም ድርድር እንዲገባ የቅርብ ክትትል እንዲያደርጉ አሸብር ኃ/ጊዮርጊስ (ዶ/ር) የተባሉ የም/ቤት አባል የጠየቁ ሲሆን፤ ለዚህም ምክንያት ሲያነሱ ችግሮችን እንዲፈቱ የተቋቋሙ ኮሚሽኖች ውጤታማ አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሀገሪቱ ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች ያሉት ሌላኛው የም/ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ለዚህም መንግስትን ተጠያቂ አድርገዋል።
"ተጠያቂው ብልጽግናና የእርስዎ አመራር ነው” ያሉት የም/ቤቱ አባሉ፤ “ሀገራዊ የቀውስ መፍትሄ አፈላላጊ ጉባኤ" እንዲቋቋም ጠይቀዋል።
ለጥያቄዎቹ መልስና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ከህውሓትና “ከኦነግ ሸኔ” ጋር የተደረገውን ድርድር በመጥቀስ ለድርድር የመንግስት በሩ ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።
የሀገሪቱ ሰላም እጦት ምንጩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ "ጽንፍ የወጣ ፖለቲካ፣ የወል እውነት ማጣት እንዲሁም ስራ አጥነት" ለአለመረጋጋቱ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
"አዎ ከለውጡ በኋላ ፈተና በዝቷል። ግን ፈተናው እያዳከመን አይደለም። እንደ ወርቅ አጠንክሮ ያወጣን ነው። ተቋማትን እየገነባን ነው። ኢኮኖሚያዊ እድገት እያመጣን፤ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ትበተናለች የሚለው ቀርቶ አሁን ኢትዮጵያ የማትፈርስ ሀገር ናት። ችግር አለ ግን ችግሩ እያጠፋን አይደለም። የችግሩ መንስኤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነው" ብለዋል።
ችግሮቹ ህግ በማስከበርና በድርድር እንደሚመለስም ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ "በችግር ውስጥ እድል፤ በነውጥ ውስጥ ለውጥን ብናይ" ሲሉም አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለ ሸገር ከተማ ምን አሉ?
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሸገር ከተማ ቤት ፈረሳን በሚመለከት መሬትን "የህዝብና የመንግስት" የማድረግ ጥረት አካል ነው ብለዋል
ቤታቸው የፈረሰባቸው "ህጋዊ" ሰዎች ካሳ እንደሚያስፈልጋቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ወደፊት በሚሰሩ እንደ ጋራ መኖሪያ ቤቶች ባሉ መርሃ-ግብሮች ሊታይ እንደሚችል ጠቁመዋል።