በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ጠ/ሚ ዐቢይ ነገ ለኢጋድ ሀገራት መሪዎች ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል
የኢትዮጵያን ውስጣዊ ጉዳይ ጨምሮ የኬንያ እና ሶማሊያ አለመግባባት ዋነኛ የውይይት አጀንዳዎች ይሆናሉ
የኢጋድ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ነገ በጅቡቲ ይካሔዳል
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) 38ኛ ልዩ ጉባዔውን ነገ ዋና መሥሪያ ቤቱ በሚገኝበት ጅቡቲ ያደርጋል፡፡
የክፍለ አህጉሩ ቀጣናዊ ተቋም ፣ በመሪዎች ደረጃ በሚያደርገው በነገ ጉባዔው በኬንያና ሶማሊያ እሰጥ አገባ ፣ በኢትዮጵያ በተካሄደው የሕግ ማስከበር ሂደት ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን የድንበር ላይ ቀውስ እንዲሁም በኤርትራ እና በጅቡቲ መካከል ባለው የቆየ ግጭት ዙሪያ እንደሚወያይ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስበር ሥራ እና አሁን ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች ሪፖርት እንደሚያቀርቡ የወቅቱ ሊቀመንበር አብደላ ሀምዶክ ከቀናት በፊት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በነገው ጉባዔ ከሰሞኑ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸው የሻከረው ሶማሊያና ኬንያ ጉዳይም አንዱ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በውስጥ ጉዳዬ በግልጽ ጣልቃ ገብታብኛለች በሚል ሶማሊያ ከኬንያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማቋረጧን የገለጸች ሲሆን ዲፕሎማቶቿም ከናይሮቢ እንዲመለሱ አዛለች፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ይገኙበታል ተብሎ በሚጠበቀው በጅቡቲው ጉባዔ የደቡብ ሰዳን የሰላም ጉዳይ ላይም ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
የአሁኑ የኢጋድ ስብሰባ አሜሪካ ሱዳንን ሽብርን በመንግስት ደረጃ ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ከሰረዘች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ መሆኑ ለቀጣናው በአወንታዊነት የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡
ኢጋድ በአውሮፓውያኑ 1999 የተቋቋመ እና ዋና መሥሪያ ቤቱን በጅቡቲ የሚገኝ ኢትዮጵያን፣ ጅቡቲን ፣ ኬንያን፣ ሶማሊያን ፣ ሱዳንን ፣ ደቡብ ሱዳንን ፣ ኡጋንዳ እና ኤርትራን በአባልነት ያቀፈ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ተቋም ነው፡፡