ጠ/ሚ ዐቢይ ከቀናት በኋላ በጅቡቲ ለኢጋድ መሪዎች ሪፖርት እንደሚያቀርቡ የሱዳን ጠ/ሚ ገለጹ
ከትናንት በስቲያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ጠ/ሚ ሀምዶክ ለምን ወዲያው ተመለሱ?
የሱዳን ጠ/ሚኒስትር በኢትዮጵያ የነበራቸው ጉብኝት ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከትናንት በስቲያ ታህሣሥ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት መምጣታቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለት ቀናት እንደሚቆዩ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም በመጡበት ዕለት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ይህም በተለያዩ አካላት እና ሚዲያዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን በተመለከተ ትናንት ምሽት መግለጫ የሰጡት ሀምዶክ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ስኬታማ ቆይታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ የጉብኝታቸውን ዓላማ ማሳካታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
“በሚዲያዎች የተንሸራሸሩ አሉታዊ ሀሳቦች ሁሉ አሉባልታዎች ናቸው” ብለዋል ሀምዶክ በመግለጫቸው፡፡ ከአቀባበል ጀምሮ ጠ/ሚ ዐቢይ ራሳቸው በሚያሽከረክሩት መኪና ተቀብለዋቸው እንዳስተናገዷቸው እና በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች መምከራቸውን አንስተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ በሚካሔደው የጅቡቲ ስብሰባ ፣ በህዳሴ ግድብ ቀጣይ ድርድር እንዲሁም በኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡
በትግራይ ክልል የተፈጠረውን እና አሁን ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በቀጣዩ እሁድ በጅቡቲ ለኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች ሪፖርት እንደሚያቀርቡም ጠ/ሚ ሀምዶክ ተናግረዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ “እስካሁን ከነበረኝ ጉብኝት የአሁኑ ይበልጥ የተሳካ ነበር” ያሉት ጠ/ሚ ሀምዶክ “ከዚህ በተቃራኒ የሚባሉ ነገሮች ሀሰት ናቸው” ብለዋል፡፡ “ ‘አየር ማረፊያ እንደደረሰ ተባረረ’ እስከመባል የሀሰት መረጃዎች ተናፍሰዋል” ያሉት ሀምዶክ ይህ የፈጠራ ወሬ እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡
ጉብኝታቸው ለሁለት ቀናት የታሰበ ቢሆንም “ከአየር ማረፊያው ወደ ቤተመንግስት በመጓዝ ላይ እንዳለን ፣ በሁለቱም ሀገራት ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በአጀንዳዎቻችን ላይ ተነጋግረን ሌላው ጉብኝት እንዲቀር እኔ ባቀረብኩት ሀሳብ ተግባብተን ነው የሁለተኛው ቀን ጉብኝት የቀረው” ብለዋል፡፡ “በመሆኑም በአጀንዳዎቻችን ላይ ስኬታማ ውይይት አድርገን ሌሎች ተጨማሪ የገሁብኝት አጀንዳዎችን ሰርዘናል” ነው ያሉት፡፡
ሱዳን በችግር ላይ በነበረችበት ጊዜ ኢትዮጵያ በቀዳሚነት የደረሰችላት መሆኑን በማስታወስ በኢትዮጵያ ችግር ጊዜም ሱዳን ደጋፊዋ መሆኗን ለማሳየት የተደረገ ጉብኝት መሆኑንም ጠ/ሚ ሀምዶክ ገልጸዋል፡፡
ጠ/ሚ ሀምዶክ ፣ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ቀውስ ከተከሰተ በኋላ ጉብኝት ያደረጉ የመጀመሪያው የውጭ ሀገር መሪ ናቸው፡፡
ሀምዶክ በመጡበት ዕለት ከሰዓት ወደ ካርቱም ሲመለሱ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ደግሞ መቀሌ አቅንተው ከመከላከያ ሠራዊት ጦር መኮንኖች እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር መወያየታቸው ይታወሳል፡፡