ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ዳውሮ ዞን አቅንተው በገበታ ለሀገር መርሃ-ግብር የኮይሻ ፕሮጀክትን አስጀመሩ
የኮይሻ ፕሮጀክትን በገበታ ለሀገር መርሃ-ግብር ከሚለሙ ሦስት ፕሮጄክቶች አንዱ ነው
ለገበታ ለሀገር 4.2 ቢሊዮን ብር መሰበሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ዳውሮ ዞን ገብተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገበታ ለሀገር መርሃ-ግብር የኮይሻ ፕሮጀክትን የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታን ለማስጀመር በዞኑ ሎማ ወረዳ ሲደርሱ የአካባቢው ህብረተሰብ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡
በዋሩማ ቀበሌ ለሚገኘው እና የፕሮጀክቱ አካል ለሆነው "ንጉስ ሃላላ ካብ ክላስተር" የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ለገበታ ለሀገር መርሃ-ግብር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 3 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ይሁን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ፣ ለገበታ ለሀገር 4.2 ቢሊዮን ብር መሰበሰቡን ነው ያስታወቁት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “3 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ አቅደን ጀመርን፤ እናንተ ደግሞ ኮይሻን፣ ወንጪን እና ጎርጎራን ለማልማት 4.2 ቢሊየን ብር እንዲሰበሰብ አደረጋችሁ” ሲሉ ገልጸዋል።
“በህብር ወዳሰብነው እንደርሳለን” ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ “ገበታ ለሀገር እውን እንዲሆን የበኩላችሁን ላዋጣችሁ በሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጭ የምትገኙ መላው ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡