“የቀጣናው መረጋጋት በእድገት እና ልማት ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ኬንያ እና ሶማሊያ ከሰሞኑ ወደ ሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መግባታቸው የሚታወቅ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኬንያ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ መሪዎች ጋር መወያየታቸውን አስታወቀዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኬንያ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ፕሬዝዳንቶች ጋር ተወያዩ፡፡
ለ38ኛው የኢጋድ ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ጅቡቲ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣናችን (ምስራቅ አፍሪካ) ያለው መረጋጋት በእድገት እና ልማት ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል፡፡
እንደ መሪ በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው በቀጣናው አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ርብቃ ንያንዴንግ ደ ማቢዮርም ጋር ሁለትዮሽንና የደቡብ ሱዳን ሰላምን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በባህር የድንበር ይገባኛል ጉዳዮች ላይ ወትሮውኑ ይወዛገቡ የነበሩት ኬንያ እና ሶማሊያ ከሰሞኑ ወደ ሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መግባታቸው ይታወቃል፡፡
የኬንያን አምባሳደር እስከማባረር የደረሰችው ሶማሊያ የናይሮቢ ኤምባሲዋን እስከመዝጋት ደርሳም ተመልክተናል፡፡
በኢጋድ አባል ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያጠናክሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ያስታወቁት ዶ/ር ዐቢይ ይህን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከመሪዎቹ ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል ከሱዳንና ሶማሊያ መሪዎች ጋር ያደረጉትን ምክክር በተመለከተ አል ዐይን አማርኛ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡