ጠ/ሚ ዐቢይ ኢትዮጵያውያን "መቻቻልና አብሮነት እንዲያሸንፍ" እንዲጸልዩ ጥሪ አቀረቡ
ዶ/ር ዐቢይ "ተሸናፊ ውርስ ሊያሳምመን እንጂ ሊያሸንፈን አይችልም"ም ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን ዛፎችን እንዲተክሉም ጥሪ አቅርበዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን "መቻቻልና አብሮነት እንዲያሸንፍ" እንዲጸልዩ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ነባር ችግሮች የኢትዮጵያን መከራ ለማርዘም እየታገሏት" እንደሆነ በመግለጽ "በዚህ እሑድ ሁላችንም መቻቻልና አብሮነት እንዲያሸንፍ እንጸልይ" ብለዋል።
በዛሬ የሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ/ም የማህበራዊ ሚዲያ መልዕክታቸው "ኢትዮጵያ ከነባር ችግሮቿ ተላቅቃ በተስፋዋ ጎዳና እንድትገሠግሥ እየታገልን ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ያለፈው ችግሯ ውርስ መከራችንን ሊያረዝመው ይታገለናል፤ እኛ ደግሞ ተስፋችንን ለማለምለም እንታገላለን" ብለዋል በችግሮች መዋጥ ይበልጥ መከራን እንደሚያነግስ በመጠቆም፡፡
ለተስፋ በመታገል መከራ ላይ መንገስ እንደሚቻል የገለጹም ሲሆን "በዚህ እሑድ ሁላችንም መቻቻልና አብሮነት እንዲያሸንፍ እንጸልይ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ነገን ብሩህ ለማድረግ ሁሉም ወጥቶ ዛፍ እንዲተክልም ነው ዶ/ር ዐቢይ ጥሪ ያቀረቡት፡፡
"ተሸናፊው ውርስ ችግር ሊያሳምመን እንጂ ሊያሸንፈን አይችልም" የሚል መልዕክትንም አስፍረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ "የኢትዮጵያን መከራ ለማርዘም እየታገሏት" ነው ስላሏቸው ነባር ችግሮች ምንነት በውል አላስቀመጡም በመልዕክታቸው፡፡
ሆኖም ባለፍነው አርብም የጁምዓ ዕለት፤ ዕለቱ "የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ነፍሱን በይቅር ባይነት አንጽቶ፣ ልብሱንም በመልካም መዓዛዎች አጥርቶ በፈጣሪው ቤት የሚሰባሰብበት የተወደደ ዕለት" እንደሆነ በማስታወስ ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገሩ ሰላም የሚጸልይበት እንዲሁም ለትውልድ የሚተርፍ መልካም አሻራ የሚያሳርፍበት እንዲሆን ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
"ለመጪው ትውልድ የምናስረክባት ኢትዮጵያ ሁሉም በሰላም የሚኖርባትና ለምለም ምድር ለማድረግ አብረን እንቁም" ሲሉም ነበር በዕለቱ ጥሪውን ያቀረቡት።
የአረንጓዴ ዐሻራ አራተኛ ዓመት መርሀ ግብር ከሰሞኑ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ በሚገኙ ቶሌ እና ሌሎችም ቀበሌዎች ማንነትን መሰረት አድርጎ በተፈጸመው ጥቃት በርካቶች መገደላቸውና መፈናቀላቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡
ተመድን መሰል ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጭምር ግድያው ተጣርቶ ወንጀለኞች እንዲጠየቁ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡
የአብን የምክር ቤት አባላት “የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት አንታገስም” ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ ከግድያው ጋር በተያያዘ ለፓርላማው ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቃቸውም የሚታወስ ነው፡፡