"የእምነት ተቋማት ህግ ወጥቶ ኦዲት መደረግ አለባቸው" - ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት እስካሁን እንዳላገኙም ነው የተናገሩት
በፍትህ ተቋማት ጠንካራ የለውጥ ስራዎች እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል
ዛሬ ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) "የእምነት ተቋማት ህግ ወጥቶ ኦዲት መደረግ አለባቸው" ሲሉ ተናገሩ፡፡
በውስጣችን ያለውንን ሌብነት ለማጽዳት እየሞከርን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባሩ እየተበራከተ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም አንደኛ ሌቦች ዳኞች ናቸው ያሉ ሲሆን ፍርድ ቤት አካባቢ ከፍተኛ የለውጥ (ሪፎርም) ስራዎች እንደሚሰሩና እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
"ዳኛ፣ ዐቃቤ ህግ፣ ፖሊስ ኦዲተር ሳይቀር ሌባ ሆኗል" ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለምክር ቤቱ ያሉት፡፡
በመሆኑም ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ኦዲተር እንዲሁም የጸረ ሙስና ተቋማትን ጨምሮ በሌሎች የፍትህ ተቋማት ሌብነትን ለማስቀረት የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ የእምነት ተቋማት ዋና የሌብነት ምንጭ ናቸውም ነው ያሉት፡፡ ህግ አውጥተን ኦዲት መደረግ አለባቸውም ብለዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት "ታክስ እንኳን ባይከፍሉ እያንዳንዱ ሃብት ለተቋሙ መዋሉ መረጋገጥ አለበት" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒትሩ " ግለሰቦች ሃብት እያከማቹ እንደፈለጉ የሚያተራምሱበት ሃገር አይኖርም ከአሁን በኋላ" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
የሚሰበሰበው ሃብት ኦዲት ተደርጎ ለልማት የሚውልበት መንገድ መፈለግ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ሁሉን አካታች ብሄራዊ ምክክርን በተመለከተ ቁርጠኛ ስለመሆኑ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
"ብሔራዊ ምክክሩ ክርክር ሳይሆን ሊያግባባ በሚችል መልኩ ህዝብ ወሳኝ ሆኖ ተቋሙ ተዓማኒነት እንዲኖረው ተደርጎ እንዲቋቋም አድርገናል" ያሉም ሲሆን ኮሚሽኑ በራሱ አጀንዳ እና ተሳታፊዎችን እንዲመርጥ ነጻ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
ሆኖም እስካሁን ኮሚሽኑን እንዳላገኙት ነው የገለጹት፡፡
የኮሚሽኑ አባላት ከታገዙ ሊያሳኩት እንደሚችሉ በመጠቆምም ምክክሩ አድካሚ በመሆኑ ሁላችንም ለመጠቀምና ሃገራችንን ለመጥቀም አጋጣሚውን እንጠቀምበት ሲሉ ለስኬታማነቱ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሰፊ ተጽእኖ አለው ስላሉት ስለ ማህበራዊ ሚዲያ ጎጂ ተጽእኖው ሊቀነስ የሚችልበት መንገድ ሊፈለግ እንደሚገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከለውጡ በኋላ የሚዲያ አፈና አለ የሚባለው ውሸት ነው ብለዋል፡፡ ከለውጡ በኋላ ያለው ሚዲያ በፊት ከነበረው በአንድ ሺ እጥፍ የሚበልጥ እንደሆነም ተናግረዋል፤ "ደሞ ሚዲያ አሸን አይደለም እንዴ?" ሲሉ የሚጠይቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
"ሀገርን እንደ እቁብ ታይታ" ተረኝነት አለ ሊባል እንደማይገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት አስተዳደር የብሔር ተዋጽኦ ሁሉን አቀፍ መሆኑን፣ በፌደራል ሠራተኞች ደረጃም ጭምር አይተናል ብለዋል፤ የልማት ድርጅቶች ሳይቀሩ መፈተሸቸውን በመጠቆም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሰው ኃይል የብሔር ስብጥርን በማሳያነት በማንሳትም አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ምክር ቤቱ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ወስዶ የብሔር፣ የጾታ፣ የእምነት እና የመሳሰለውን ተዋጽዖን የተመለከተ ሕግ አውጥቶ በዚያ መሠረት ቢያስፈጽም የሚነሳውን ጥያቄ ሊቀርፍ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡