ኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ እዳ መክፈል አልቻለችም መባሉ እጅ የመጠምዘዝ ሙከራ ነው - ጠ/ሚ አብይ
33 ሚሊየን ዶላር የዩሮ ቦንድ ወለዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለት ቀን ገቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ መንግስት የውጭ እዳን በመክፈል ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል ብለዋል
ባለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ 9 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር እዳ መክፈሏን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ስትወስድ የነበረውን ብድር ከ”አራጣ” ጋር ያመሳሰሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ባለፉት አምስት አመታት ሀገሪቱን በብዙ በጎዳው “ኮሜርሻል ሎን” አንድም ብድር አልወሰድንም ብለዋል።
ከ2011 እስከ 2015 ባሉት አምስት አመታትም 9 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የውጭ እዳ መከፈሉን ነው ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ ያነሱት።
የኢትዮጵያ የውጭ እዳ ከአምስት አመት በፊት ከሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ወይም ጂዲፒ 32 በመቶ እንደነበር በማውሳትም አሁን ላይ ወደ 17 በመቶ ዝቅ ብሏል ብለዋል።
የኢፌዴሪ መንግስት እቅድ የውጭ እዳን ከ10 በመቶ ማውረድ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከዘጠኝ አመት በፊት በዓለም ገበያ ቦንድ በመሸጥ ላገኘችው የ1 ቢሊየን ዶላር ብድር መክፈል የነበረባትን 33 ሚሊየን ዶላር ወለድ መክፈል አለመቻሏ መገለጹ ይታወሳል።
ይህም ብድራቸውን መክፈል ካልቻሉ እንደ ጋና እና ዛምቢያ ያሉ ሀገራት ጎራ እንድትሰለፍ አድርጓታል። ይህም በቀጣይ ብድር እንዳታገኝ ሊያደርጋት እንደሚችል ሲገለጽ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ግን ባለፉት አምስት አመታት 9 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር እዳ የከፈለች ሀገር የ33 ሚሊየን ዶላር ወለድ መክፈል የሚከብዳት ሀገር አይደለችም ብለዋል።
የዩሮ ቦንድ 33 ሚሊየን ዶላር ወለዱ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለት ቀን ገቢ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ባለፉት አምስት ወራት 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ እቃዎችን ከውጭ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰዋል።
የዩሮ ቦንድ ወለዱን መክፈል አልቻሉም በሚል”እጃችን ለመጠምዘዝ” የሚደረግ ሙከራ አለም ነው ያሉት።
የገንዘብ ሚኒስቴር እዳው ያልተከፈለው “አበዳሪዎችን እኩል ለማስተናገድ ነው” እንጂ ኢትዮጵያ አቅም አጥሯት እንዳልሆነ መጥቀሱ ይታወሳል።
የሀገሪቱ የውጪ ብድር መጠን 28 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ማሳወቁም አይዘነጋም።