አሜሪካ ኮንግረስ ለእስራኤል እና ዩክሬን ተጨማሪ እርዳታ እንዳይሰጥ ባያግድ የብድር መጠኑ ከዚህም ከፍ ሊል ይችል ነበር ተብሏል
የአሜሪካ ብሔራዊ እዳ መጠን 34 ትሪሊዮን ዶላር አለፈ፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ የእዳ መጠኗ ከ34 ትሪሊዮን ማለፉን የሀገሪቱ ግምጃ ቤት በድረገጹ አስታውቋል።
የሀገሪቱ የእዳ መጠን በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የዋጋ ግሽበት መፈጠሩ፣ ለዩክሬን እና እስራኤል የተሰጠው እርዳታ በየጊዜው መጨመር የመንግስት የሚበደረውን የገንዘብ መጠን እንዲጨምር አድርጓል ተብሏል።
የአሜሪካ መንግስት እዳ መጠን ባሳለፍነው ጥር ላይ 31 ትሪሊዮን ደርሶ የነበረ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ተጨማሪ 2 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር ተጨማሪ ብድር መበደሩ ተገልጿል።
ለዩክሬን እና እስራኤል የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ ይደረግ አይደረግ በሚል የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ከስምምነት ላይ አለመድረሳቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ በፊት በተለይም የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች በስፋት የነገር የነበረው የዩክሬን ጦር መሳሪያ ድጋፍ ይቁም የሚለውን ሀሳብ ዲሞክራቶችም እየተቀበሉት ይገኛሉ ተብሏል፡፡
አለመስማማቱን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መንግስታቸው እንዳይዘጋ በሚል ለቁልፍ ተቋማት እና ስራዎች ከሚደረግ ወጪ በስተቀር አዲስ በጀት እንዳይጸድቅ ከሪፐብሊካን ተወካዮች ጋር ተስማምተዋል፡፡
የአሜሪካ እዳ ለምን 31 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር ደረሰ?
ዩክሬን በበኩሏ ከአሜሪካ ተጨማሪ ገንዘብ እና ጦር መሳሪያ እንዲሰጣቸው በመወትወት ላይ ሲሆኑ ሀገራቸው በሩሲያ ከተሸነፈች ሽንፈቱ ከኪቭ በተጨማሪ የኔቶም ይሆናል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በፈረንጆቹ 2014 ወደ ሩሲያ የተቀላቀለችው ክሪሚያን በተያዘው 2024 ዓመት ከሩሲያ እንደሚነጥሉ በአዲስ ዓመት ንግግራቸው ላይ ቃል ገብተዋል፡፡
ለዚህ እቅዳቸውም ጀርመን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ድጋፍ እንድታደርግላት ፕሬዝዳንቱ የጠየቁ ቢሆንም ጀርመን ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች፡፡