ጠ/ሚ ዐቢይ “በሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ስለሚሰፍንበት ሁኔታ ተወያይተናል” ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት አዛዥ ጀነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሃሜቲ) ጋር ተወያዩ።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት አዛዥ ጄነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሃሜቲ) አዲስ አበባ በዛሬው እለት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ጄነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሃሜቲ) በአዲስ አበባ ቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተገናኝተው ተወያተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው “ዛሬ መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎን ተቀብዬ በሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ስለሚሰፍንበት ሁኔታ ተወያይተናል” ብለዋል።
ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ከሱዳን ብሔራዊ ጦር ጋር እየተዋጉ ያሉት የፈጥኖ ደራሽ ሀይል አዛዥ ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ወይም ሄመቲ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት በኡጋንዳ ቆይታ አድርገው ነበር።
ጀነራል ሄመቲ ከኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ጋር እንደተወያዩ የተገለጸ ሲሆን ጦርነቱን በውይይት መፍታት ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደተነጋገሩም ፕሬዝዳንቱ በኤክስ አካውንታቸው ላይ አስፍረዋል።
ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒም ሱዳናዊን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ገልጸው ኡጋንዳ የሱዳን ጦርነት እንዲቆም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ለጀነራል ሄመቲ ነግረዋቸዋልም ተብሏል።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሱዳን ጦርነት እንዲቆም ተፋላሚ ወገኖችን ፊት ለፊት ከማገናኘት ባለፈ የኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መሪዎች መፍትሄ እንዲያፈላልጉ መሾሙ ይታወሳል።
ኢጋድ የሱዳን ብሄራዊ ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች አዛዥ ጀነራል ሄመቲን ፊት ለፊት እንዲገናኙ ለዛሬ ቀጠሮ የነበረው ቢሆንም ይህ ፕሮግራምን ወደ ጥር ወር አሸጋግሮታል፡፡
ዘጠኝ ወር የሞላው የሱዳን ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ እና ወደ ስምምነት እንዲመጣ የተለያዩ አካላት ተጽዕኖ በማድረግ ላይ ቢሆኑ በጀነራል ሄመቲ የሚመራው ጦር የሱዳን ጦር ማዘዣዎችን በመቆጣጠር ላይ ይገኛል፡፡
የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሃን በበኩላቸው የጦሩ ቁልፍ ማዘዣዎች በቀላሉ በፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች እንዲያዝ ያደረጉ አመራሮችን እንደሚቀጡ መዛታቸው ይታወሳል፡፡