የሱዳን ጦር መሪ ቁልፍ ከተማ የለቀቁ ወታደራዊ አዛዦችን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ገለጹ
በሀገሪቱ ለስምንት ወራት ከዘለቀው ውጊያ መሸሻ ቦታ ተደርጋ ከምታተየው የአልገዚራ ግዛት 300ሺ ሰዎች ለመፈናቀል ተገደዋል
የሱዳን ጦር አዛዦ ጀነራል አልቡርሃን የዋድ መዳኒ ከተማ መያዟን ተከትሎ "ግዴለሽ" ያሏቸውን የጦር አዛዦች ተቆጥተዋል
የሰዳን ጦር መሪ ቁልፍ ከተማ የለቀቁ ወታደራዊ አዛዦችን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ገለጹ።
የሱዳን ጦር አዛዦ ጀነራል አልቡርሃን በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ የሚመሩት ጦር ቁልፍ የተባለችውን የዋድ መዳኒ ከተማ መያዙን ተከትሎ "ግዴለሽ" ያሏቸውን የጦር አዛዦች ተቆጥተዋል።
ጦሩ ሳይዋጋ የአልገዚራን ዋና ከተማ በመልቀቁ ትችት አጋጥሞታል።
በሀገሪቱ ለስምንት ወራት ከዘለቀው ውጊያ መሸሻ ቦታ ተደርጋ ከምታተየው የአልገዚራ ግዛት 300ሺ ሰዎች ለመፈናቀል ተገደዋል።
የዋድ መዳኒ ከተማ ከተያዘች ከአራት ቀናት በኋላ ጀነራል አል ቡርሃን ስለጉዳዩ በአደባባይ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ጀነራል አል ቡርሃን "እያንዳንዱን ግዴለሽ የሆነ አዛዥ ተጠያቂ እናደርጋለን። ከተማዋ እንድትለቀቅ ያደረጉ ሁሉ ያለምህረት ተጠያቂ ይደረጋሉ" ብለዋል።
የሱዳን ጦር ተቀናቃኝ የሆነው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እንዴት ሊገባ እንደቻለ እንደሚመረምረው ገልጿል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አጠቃላይ የአልገዚራ ግዛትን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል። ግጭቱ ወደ ጎረቤት ግዛቶች ይሰፋፋል በማል ስጋት የእርዳታ ሰራተኞች ከአጎራባች ግዛቶች ለቀው በመውጣት ላይ ይገኛሉ።
በዋና ከተማዋ ካርቱም ግጭት በተነሳ ጊዜ ተሰደው ወደ አልገዚራ የመጡ ስደተኞች በድጋሚ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ከአልገዚራ በስተምስራቅ በኩል ያለችውን የገዳርፍ ግዛት ለመያዝ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ሱዳንን ለሶስት አስርት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ የመሩት ኦመር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ከተመሰረተው የሲቪል መንግስት ጋር ሲያስተዳድሩ በነበሩ ጀነራሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ሀገሪቱን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከቷታል።
ከተቀሰቀሰ ስምንት ወራትን ባስቆጠሰው ጦርነት በሺዎች ተገድለዋል፣ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።