አትሌቷ በ48 ስአታት ውስጥ ረጅም ርቀት በመሮጥ የአለም ክብረወሰንን በያዘች ማግስት በቅሌት መዝገብ ያሰፈረ ድርጊትን መፈጸሙ አነጋጋሪ ሆኗል
የማራቶን ውድድሯን በመኪና ያጋመሰችው አትሌት ሜዳልያዋን ተነጠቀች።
የ47 አመቷ ስኮትላንዳዊ ጆሲያ ዛክሬውስኪ በብሪታንያ ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደ የ80 ኪሎሜትር የሩጫ ውድድር 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
መነሻውን ማንቸስተር አድርጎ በሊቨርፑል በተጠናቀቀው ውድድር የነሃስ ሜዳሊያ በመሸለሟም ደስታዋ ከፍ ብሎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ምስሎችን አጋርታለች።
ያልጠበቀችውን ድል ማግኘቷ ቢያስፈነድቃትም ስጋት ያጫረባት ጉዳይ ግን ነበር፤ የውድድሩን ህግ መተላለፏን ባትዘነጋውም እንዳይደረበት ግን መጸለይ መርጣ ደስታዋን እያጣጣመች ነበር።
የፈራችው ነገር ግን አልቀረላትም፤ ስሟን የሚያጎድፈው ተግባሯ በአንገቷ ያጠለቀችው ሜዳልያንም እንድትመልስ ግድ ሆኗል።
ዛክሬውስኪን ለዚህ ያበቃት የውድድሩ አዘጋጆች ከሁለት ማራቶን የማይተናነሰውን (80 ኪሎሜትር) ውድድር ቪዲዮ እና የአትሌቶቹን ፍጥነት ሲመለከቱ ነው።
ስኮትላንዳዊቷ አትሌት በውድድሩ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በስአት 56 ኪሎሜትር የመሸምጠጧ ነገር አጃኢብ ያሰኛቸዋል፤ ፍጥነቷ ጃማይካዊውን ዩዜን ቦልት ተክታ የአለማችን ፈጣን ሯጭ የሚያደርጋት ነውና።
ጉዳዩ ያጠራጠራቸው የውድድሩ አዘጋጆችም ቪዲዮ ሲመለከቱ ዛክሬውስኪ ውድድሩን አቋርጣ ወጥታ ዳግም የሸመጠጠችበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል ጥርጣሬያቸው ያይላል።
የአይን እማኞችን አነጋግረው አትሌቷን ለማብራሪያ ሲጠሯትም የተፈጠረውን ነገር ሳትደብቅ ትናገራለች፤ “ውድድሩ ሲጋመስ በጣም የህመም ስሜት ተሰማኝ፤ አቋርጨውም ወደ ጓደኛዬ መኪና ውስጥ ገባሁ፤ በዚህ ወቅትም ለምን በመኪና አልሸኝሽም የሚለውን ሃሳብ ተቀበልኩ” ትላለች አትሌቷ።
የውድድሩ ማጠናቀቂያ ሲቃረብ ከመኪና ወርዳ መሮጥ መጀመሯን የምትገልጸው ዛክሬውስኪ፥ “አሞኝ መኪና ውስጥ ነበርኩ ስላቸው (ተቆጣጣሪዎቹን) ውድድሩንማ ማጠናቀቅ አለብሽ የሚል ሞራል ሰጡኝ” ትላለች።
ይሁን እንጂ በውድድሩ የነሃስ ሜዳልያ የሚያስገኝ ውጤት እንደምታስመዘግብ በፍጹም አለመጠበቋን በመጥቀስ እየመራች ያለችውን አትሌት ስትመለከት መቅደም አለመፈለጓንና ማጠናቀቅ ብቻ ግቧ እንደነበርም ታነሳለች።
የ80 ኪሎሜትር የሩጫ ውድድሩን ጀምራው በመኪና አጋምሳ የጨረሰችው ጆሲያ ዛክሬውስኪ ያደረገችው ፍጹም ስህተትና ሙያዊ ስነምግባርን ያልጠበቀ መሆኑን አምናበት ጭምር የነሃስ ሜዳልያዋን መልሳለች።
ባታምንበትም ሜዳልያውን መነጠቋ አይቀርም የሚሉ የስፖርት ቤተሰቦች ግን አትሌቷ አዘጋጆቿ ሳይጠሯት በፈቃዷ ሄዳ ሜዳልያውን መመለስ ነበረባት በሚል እየተቃወሟት መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
በ48 ስአታት ውስጥ ረጅም ርቀት በመሮጥ የአለም ክብረወሰንን ከሳምንታት በፊት የያዘችው ጆሲያ ዛክሬውስኪ ስሟ በቅሌት መዝገብ ውስጥ መስፈር እንዳልነበረበትም የሚያነሱ በርካታ ናቸው።