"የኢትዮጵያ አርሶአደር ከተሜው እንዲራብ መፍቀድ የለበትም” -ጠ/ሚ አብይ
ዋጋ ይጨምራል በሚል 1 ሺህ ኩንታል እህል በቤቱ ያከማቸ አርሶ አደር መገኘቱንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት
መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ለነዳጅ ብቻ 50 ቢሊየን ብር ድጎማ ማድረጉንም ጠቅሰዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት አባላት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች ውስጥ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የኑሮ ውድነት አንዱ ነው።
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው የጤፍ እና ስንዴ ዋጋን ለማረጋጋት ምን እየተሰራ ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ለጤፍ ዋጋ ንረቱ የምርት እጥረት ምክንያት አይሆንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥
የዋጋ ጭማሪ ይከሰታል በሚል ምርት የሚያከማቹ አካላት የጤፍ ዋጋን እንዲንር አድርገዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዋጋ ንረቱ አርሶ አደሮችንም ወቅሰዋል፤ ፍትሃዊ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው በሚል።
“1 ሺህ ኩንታል በቤቱ ያስቀመጠ አርሶ አደር አለ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ የኢትዮጵያ አርሶአደር የከተማ ህዝብ እንዲራብ መፍቀድ የለበትም ሲሉም ነው ያሳሰቡት።
በመንግስት በኩልም እንደ ኬላ መዝጋትና የመንገድ ላይ ፍተሻን ማብዛት ያሉ ችግሮች ለዋጋ ንረቱ አንዱ ምክንያት መሆኑንም አምነዋል።
ከስንዴ ጋር በተያያዘም የምክር ቤቱ አባላት በቂ ምርት ሳይኖረን ወደ ውጭ መላክ መጀመራችን ምን ያህል አሳማኝ ነው? የሚል ጥያቄ ቀርቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱም “የአቅርቦት ችግር የለም፤ በበጋ መስኖ ከታረሰው 1 ሚሊየን ሄክታር መሬትም 40 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል” ብለዋል።
ስንዴ ወደ ውጭ መላክ ከተጀመረ ወዲህም ኢትዮጵያ ለስንዴ ግዥ ዶላር አለማውጣቷን በስኬትነት አንስተውታል።
ዋነኛው ችግር ዋጋ ይጨምራል በሚል እሳቤ ምርቱን የሚይዙ አካላት መሆናቸውን በመጥቀስም የዋጋ ንረቱ ከአቅርቦት ጋር የሚያያዝ አለመሆኑን አብራርተዋል።
በከተሞችም የምርት አቅርቦትን ለማስፋት እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት።
የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነት ስቃይ ለመቀነስ ባለፉት ስምንት ወራት ለነዳጅ 50 ቢሊየን ብር ድጎማ መደረጉንም በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።
ለማዳበሪያም 21 ቢሊየን ብር ድጎማ የተደረገ ሲሆን፥ በፍራንንኮ ቫሉታ ከገባ ዘይትና ስኳርም መንግስት ማግኘት የነበረበትን 10 ቢሊየን ብር አጥቷል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብህይ አህመድ።
በአጠቃላይ ከአለም አቀፉ ነባራዊ ሁኔታ እና ወደከተሞች ከሚደረግ ከፍተኛ ፍልሰት ጋር በተያያዘ የሚታይ ነው ያሉትን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት በከተሞች ጦአፍና ስንዴን ጨምሮ የፍጆታ እቃዎችን አቅርቦት ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል።