ጤፍን በዋናነት የሚያቀርበው አማራ ክልል ጭማሪውን ማንነታቸው አይታወቅም ካላቸው "ህገ-ወጥ ነጋዴዎች" ጋር አያይዞታል
ጤፍ ከሳምንታት በፊት ከነበረበት ዋጋ ከፍተኛ የተባለ ጭማሪ አሳይቷል።
ነጋዴዎች ጤፍ በተለይም ከሦስት ሳምንት ወዲህ ጭማሪ ማሳየቱን ማሳየቱን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
- አዲሱ መንግስት የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር ካልቻለ ሀገር ችግር ውስጥ ትገባለች- አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ይረዳል ያሉት መፍትሄ ምንድነው?
አል ዐይን ባደረገው የገበያ ቅኝትም ከወር በፊት ጤፍ በአማካኝ ከ58 እስከ 60 ብር ከነበረበት ጭማሪ አሳይቶ ከሰሞኑ በኪሎ ከ85 ብር እስከ 90 ብር እየተሸጠ ነው።
የዋጋ ጭማሪው ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት ሸማቾቾ፤ ይህም ኑሯቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል።
አይናለም የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከዚህ ቀደም 50 ኪሎ ጤፍ እንደሚሸምቱና ለመጨረሻ ጊዜ ሲገዙም ጤፍ 58 ብር እንደነበር ተናግረዋል።
"አሁን እንኳን 50 ኪሎ ይቅርና 25 ኪሎ መግዛት የምችልም አይስለኝም" ብለዋል።
"ለምን ይህን ያህል ጨመረ? ሀገር ውስጥ አይደል የሚመረተው? በጣም ከባድ ነው። ደምወዜ ጤፍ እንኳ አይገዛም አሁን። ጤፍ ብቻ ደግሞ አይበላም።" ሲሉ ተናግረዋል።
አስጨናቂ የተባሉ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ ሸማች የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ጠቅሰው "ጤፍ ለመግዛት እቁብ መግባት የግድ ሊለኝ ነው" በማለት ጫናውን ገልጸዋል።
"በልቶ ማደር ከባድ እየሆነ ነው" የሚሉት ሸማቹ፤ የዋጋ ጭማሪው ተጽዕኖ ሲገልጹት ቀላል ይመስላል ብለዋል።
አል ዐይን ያነጋገራቸው የወፍጮ ቤት ባለቤት (እህል ሻጭ) የምንጃር ጤፍ እንደያዙ ገልጸው፤ ከ82 እስከ 85 ብር እንደሚሸጡም ተናግረዋል።
ለጭማሪውም "ጤፍ እየገባ አይደለም" የሚል ምክንያት ሰጥተዋል።
አዲስ ጤፍ ካስገቡ ሦስት ሳምንት እንደሆናቸውም ገልጸዋል።
የሚልኩላቸው ደንበኛ "መንገድ ላይ ክልከላ አለ" በሚል ምርቱን እያቀረቡልን አይደለም የሚሉት ሻጩ፤ ጭማሪው ከአቅርቦት ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።
በሰንሰለቱ እጆች መበራከትና ገበያው በደላሎች መመራቱም ተጽዕኖ እንዳሳረፈ አልሸሸጉም።
የጤፍ ዋጋ መጨመርና አቅርቦትን በተመለከተ አል ዐይን የአዲስ አበባን ንግድ ቢሮ አስተያየት ቢጠይቅም መልስ አላገኘም።
ጤፍን ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ክልሎች በዋናነት የሚያቀርበው አማራ ክልል "ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ገንዘብ እየረጩ ጤፍን እያከማቹ ነው" ብሏል።
የክልሉ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፈንታው ፈጠነ፤ ባልተጠበቀ ሁኔታ ገንዘብ በባንክ እየተላከ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች እህል እየገዙ በማከማቸታቸው ምክንያት የዋጋ ጭማሪው በአማራ ክልልም ታይቷል ይላሉ።
ሰሞነኛውን የጤፍ ጉዳይ "ተገቢ ያልሆነ" የዋጋ ጭማሪ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ "ከጠበቅነው በላይና ሆኖ የማያውቅ ነው" ሲሉም ገልጸውታል።
ከወትሮው የተለየ ዋጋ የሚያስጨምር ምክንያታዊ ነገር የለም የሚሉት የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊው፤ ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸውና የጫኑት ምርት ወዴት እንደሚጓዝ የማይታወቅ ነጋዴዎች ተበራክተዋል ብለዋል።
በክልሉ ዞን ላይ የሚሰሩ አንድ የአል ዐይን ምንጭ፤ ከሰሜኑ ጦርነቱ ጋር በተያያዘ ገንዘባቸው በባንክ ታግዶ የነበሩ ነጋዴዎች አሁን ስለተለቀቀላቸው ጤፍ በስፋት እየገዙ ነው ብለዋል። ይህም የዋጋ መጨመሩ ትልቅ ምክንያት ነው ይላሉ።
ፈንታው ፈጠነ ስሙን መግለጽ ባልፈለጉት አንድ ዞን ከሰሞኑን በአንድ ቀን 220 ጤፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ተይዘው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።
"[ተሽከርካሪዎቹ] ህገ-ወጥ ስለሆኑ ነው የመለስናቸው። ህገ-ወጥ ንግድ ስለሆነ ነው። ሰነዳቸው እየታየ፤ እየተረጋገጠ ነው። የገዛው ሰው ይዞበት ወደሚሄደው አካባቢ ህጋዊ ፈቃድ ከሌለው እንመልሳለን" ብለዋል።
ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት ታይቶ አይታወቅም የተባለ ህገ-ወጥ ንግድ በክልሉ መስፋፋቱንም ኃላፊው አንስተዋል።
የጤፍ ዓመታዊ የዋጋ ጭማሪ ከአራት እስከ ስድስት በመቶ አልፎ አያውቅም የሚሉት ፈንታው ፈጠነ፤ ጤፍ ጤናማ የሚባል ግብይት ያለው የግብርና ምርት ነው ብለዋል።
የጤፍን የዋጋ ጭማሪ ለማስተካከል አማራ ክልል ግብይቱና የንግድ ሰንሰለቱ ጤናማ እንዲሆን እንዲሁም ህጋዊ ስርዓትን ለመፍጠር ቁጥጥር እያደረኩ ነው ብሏል።