በፈረንጆቹ 2021 ከነበረው የምግብ ዋጋ በ14 በመቶ ጨምሯል ተብሏል
በ2022 የፈረንጆቹ ዓመት የዓለም የምግብ ዋጋ ክብረ ወሰን አለፈ
የተመድ የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) እንደ እህል እና የአትክልት ዘይት ያሉ የምግብ ምርቶች ዓለም አቀፍ ዋጋ በተጠናቀቀው ዓመት ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል ብሏል።
ድርጅቱ እንዳለው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ ድርቅ እና ሌሎች ምክንያቶች የዋጋ ንረት እንዲባባስ ሆኗል፤ በዓለም ዙሪያ ረሃብ እንዲከሰትም አድርጓል።
መቀመጫውን ሮም ያደረገው ድርጅት የምግብ ዋጋ በፈረንጆቹ 2021 ከነበረው በ2022 በ14 በመቶ ጨምሯል ነው ያለው።
በ2022 ዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ በአማካይ 143 ነጥብ 7 ሆኖ ተመዝግቧል።
በዓመቱ የተመድ ድርጅት የምግብ ዋጋ ስነዳ ከጀመረ እ.አ.አ ከ1961 ጊዜ አንስቶ ከፍተኛውን ማስመዝገቡን ተናግሯል።
ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር የተቀሰቀሰው የሩሲያና ዩክሬንን ጦርነት የምግብ ቀውሱን አባብሶታልም ነው የተባለው።
ለዚህ ምክንያቱም ሁለቱ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የስንዴ፣ ገብስ፣ የሱፍ አበባ ዘይት እና ሌሎች ምርቶችን በተለይም በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በእስያ ክፍል ላሉ ሀገራት በማቅረብ ግንባር ቀደሞቹ ነበሩ።
ወሳኙ የጥቁር ባህር አቅርቦቶች በመስተጓጎሉም የምግብ ዋጋ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፤ የዋጋ ግሽበት፣ ድህነት እና የምግብ ዋስትና እጦት በማደግ ላይ ባሉና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተመሰረቱ ሀገራት ላይ ጠባሳውን ማሳረፉን ኤንፒአር ዘግቧል።