ጠ/ሚ ዐቢይ “የወሰን ውዝግብ ያለባቸው አካባቢዎች በህግ አግባብና በምክክር ይፈታሉ” አሉ
መንግስት “ሌብነት” ለመዋጋት በሀገራዊ ኮሚቴ ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ስለ ሰላም ስምምነቱ “ምን እንደሚመጣ ከወዲሁ መናገር አይቻልም” ብለዋል
የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄር ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ መስከረም 30፤ 2015 ዓ.ም በሁለቱ ም/ቤቶች መክፈቻ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ አሳውቀዋል።
በዚህ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከሀገሪቱ ጠቅላላ ምጣኔ-ሀብት እስከ ፖለቲካ ባህል፤ ከሰላም ስምምነቱ እስከ ደህንነት ስጋቶች ድረስ ከም/ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ ሰጠተዋል።
- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 7 ነጥብ 5 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
- ጠ/ሚ ዐቢይ “በደቡብ አፍሪካው ድርድር ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሀሳብ 100 በመቶ ተቀባይነት አግኝቷል” አሉ
የሁለት ዓመታትን ጦርነት ይገታል ተብሎ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ስለተደረሰው ሰላም ስምምነትና ስጋት ጥያቄ የተነሰላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ “ሰላምና ብልጽግናን ለማስቀጠል ሲባል ጦርነትን ማስቆም የግድ ብሏል” ብለዋል።
የኢትዮጵያን ህልውናና አንድነት የሚገዳደር ሲፈጠር ግን “መፋለም” የግድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ አሉ ያሏቸውን ሰላም የሚያስከፋቸው ኃይሎችን አሳስበዋል።
ስለ ስምምነቱ ውጤት ሲናገሩም “ምን እንደሚመጣ ከወዲሁ መናገር አይቻልም” ብለዋል። “ሌላውን ተወያይተን ፈር እናስይዘዋለን” በማለትም የስምምነቱ ቀጣይ ድርድሮችና ውይይቶች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
የምክር ቤቱ አባላት የሚያወዛግቡ አካባቢዎች በፕሪቶሪያው ስምምነት “በህገ-መንግስቱ ምላሽ ይሰጣቸዋል” መባሉ ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከወልቃይትና ራያ ጀርባ “ሽረባ” አለ ያሉ ሲሆን፤ ለዚህም የመንግስታቸው እጅ እንደሌለበት ተናግረዋል።
በተለይም የወልቃይት ጉዳይ ላይ አተኩረው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ፤ ወልቃይት “የሁለት ህዝቦች ድልድይ ነው” መሆኑን አስምረዋል።
ወዝግቡ በህግ አግባብና በምክክር የሚፈታ ነው ብለዋል። ለወልቃይት “ዲሞክራሲያዊ እድል” መሰጠት አለበት ሲሉም ውዝግቡ በስምምነት እልባት እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ መንግስታቸው ከስምምነቱ ማግስት ሶስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ያሳወቁት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ እርዳታ ማቅረብ፣ የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን መገንባት እና ተፈናቃዮች መመለስ ላይ መጠመዱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ስለ ሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ሲያብራሩ በተለይም ሸኔ ስለተባለው ታጣቂ ቡድን “ፍላጎቱ አይታወቅም” ብለዋል።
መንግስት “ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው” ብለዋል። ህገ-መንግስቱን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገገር በመንግስት በኩል አቋም እንዳለም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በታጣቂው ላይ እየተወሰደ ስላለ እርምጃ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም “ውጤቱ በተጠበቀው ልክ አመርቂ ባይሆንም ስራዎች እየተሰሩ ነው” ሲሉ እየተወሰደ ስላለ ወታደራዊ እርምጃ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ህገ-መንግስታዊ መብት ስለሆነው ተንቀሳቅሶ የመስራት መብትም ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቷል።
ህገ-መንግስታዊ መብት ስለመሆኑ ያልሸሸጉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ሆኖም ለሀገር ሰላም ሲባል መጉላላት እንደ ትልቅ ነገር መታየት እንደሌለበት ገልጸዋል።
ይልቁንም መንገደኞች ለፍተሻ እንዲተባበሩ ጠቁመዋል። “ወጣቶች ብር ተከፍሏቸው አዲስ አበባን ለማሸብት ይሞክራሉ” ያሉም ሲሆን፤ በዚህም የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እየተያዙ ነው ብለዋል።
ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አስተያየታቸውን የሰነዘሩም ሲሆን፤ “የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ችግር አለበት” ሲሉም ብቃት መመዘኛ እንዳልሆነ ተናግረዋል።። “ሰፈር ነው የሚታየው” በማለትም “ብሄር” በፖለቲካው መንገሱን ጠቁመዋል። ይህም ባህል እየሆነ ሲሄድ አደገኛ ነው በማለት “በስራ ሳይሆን በጩኸት ለውጥ ይመጣል ብለው የሚፈልጉ ሰዎች የሚያመጡት ነው” ሲሉ አሳስበዋል።
“የሽግግር መንግስት እያሉ የሚጮሁ አሉ፤ ስትጮሁ ትኖራላችውሁ፤ የኢትዮጵያን ክንፍ ነው የምትቆርጡት፤ ጥንቃቄ እናድርግ” ብለዋል።
ስለ ሙስና በሀገሪቱ መንግስት ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ “ችግርን እንደ እድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመርን ቀይ ምንጣፍ አድርገዋል” በማለት ሌብነት በመንግስት መዋቅር ስር መስደዱን ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
ሌብነት ከልምምድ እንደ መብት እየተወሰደ በመሆኑ መንግስት ተወያይቶ ሀገራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
“ክሱ ብዙ ነው፤ እጅ የማይጠቆምበት ሰው የለም” በማለትም ህዝቡ ማስረጃ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።