ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ነገ ለሚጀመረው ቀጣይ ድርድር ዋሽንግተን ገብተዋል
በግድቡ የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት ዙሪያ ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ ማዘጋጀት አልተቻለም
ነገ ረቡዕ የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ/ም (እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 12/2020) ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ ለተያዘለት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጣይ ስብሰባ የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲ.ሲ ገብተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሳምንቱን ሙሉ ከግብጽ እና ሱዳን ልዑካን ጋር የተደረገውን የህግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤት ከኢትዮጵያ ልዑካን ጋር በመሆን መገምገማቸውንም በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በማህበራዊ ገጾቻቸው አስታውቀዋል፡፡
”ቡድኑ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደረገ ቢሆንም ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ በጋራ ማዘጋጀት አለመቻሉ ታይቷል“ ያሉት አምባሳደሩ “ኢትዮጵያ በፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት የምታምን ሲሆን በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሰጥ ምንም ዓይነት ስምምነት አትፈጽምም” ሲሉም ነው በጽሁፎቻቸው ያስቀመጡት፡፡
የሶስቱ ሃገራት የውሃ ሚኒስትሮች የአሜሪካና የዓለም ባንክ ታዛቢዎች የሚታደሙት ስብሰባ ነገ ረቡዕ እንደሚጀመር በትዊተር ገጻቸው ያታወቁት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለም ይህንኑ አስረግጠው ጽፈዋል፡፡
”እኛ የኢትዮጵያ ቡድን አባላት ለሃገራችን ብሄራዊ ጥቅም ቅድሚ ሰጥተን በንቃት መስራታችንን ቀጥለናል“ የሚል መልዕክትንም አስቀምጠዋል፡፡
ከአሁን ቀደም በዋሽንግተን ሲደረጉ በነበሩ ድርድሮች የግድቡን የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ አስመልክተው በቀረቡ አራት የተለያዩ ሰነዶች ላይ የሦስቱን ሀገራት ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የአሜሪካና የአለም ባንክ ታዘቢዎች በተገኙበት ውጤታማ ድርድር ተደርጓል መባሉ ይታወሳል፡፡
በቴክኒካዊ፣ በህጋዊ፤ በግጭት አፈታት እና በትብብር ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በአጭር ጊዜ መፈራረም እንችላለን ሲሉ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ከዋሽንግተን መልስ ከቀናት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቃቸውም አይዘነጋም፡፡