የኢትዮጵያ መንግስት በሆውዚ አማጺያን የተሰነዘረውን ጥቃት ማውገዙ ይታወሳል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፣ አቡዳቢ መድረሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከክቡር ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት፤ኤሜሬትስ በሆውዚ አማጽያን ጥቃት ከተሰነዘረባት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በሆውዚ የተሰነዘረውን ጥቃት ማውገዙ ይታወሳል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአረብ ኤምሬትስ ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትትብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናሕያን ጋር በቅርቡ በስልክ ተወያይተው ነበር፡፡
በውይይቱ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሀውሲ አማጺያን ለአካባቢው ሰላም አስጊ መሆናቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ክስተቱ ለአካባቢው ሀገራት ሰላም አስጊ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ በግዛቷ ከምትወስዳቸው እርምጃዎች ጎን እንደምትቆምም ተናግረዋል፡፡
የሆውዚ አማጺያን ጥቃት ዓለም አቀፍ ህጎችን የሚጥስ እና ለአካባቢው አገራት ሰላም ጸር መሆኑንም በስልክ ውይይቱ ወቅት መነገራቸው ተገልጿል፡፡
አረብ ኤሚሬትስ ጥቃቱ ምላሽ እንደሚያሻው ገልጻ፤በሆውዚ አማጺያን ላይ አጸፋ መሰንዘሯል ይታወሳል፡፡