የጠ/ሚ ዐቢይ አስተዳደር ድጋፍ እና የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በጅማ ከተማ ተካሂዷል
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ድጋፍ እና የብልፅግና ፓርቲ የማጠቃለያ የምርጫ ቅሰቀሳ መርሃ ግብር በጅማ አለም አቀፍ ስታዲየም ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ደመቀ መኮንን፣ የህዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “በሚቀጥለው ሰኞ ሰኔ 14 2013 ዓ.ም በምናደርገው ምርጫ ዴሞክራሲን እንተክላለን፤ ዛፍም እንተክላለን” ብለዋል።
“መላው ዓለም በምርጫው እለት ይጋጫሉ ብሎ ሲጠብቀን እኛ ደግሞ እናስተምራቸዋልን” ሲሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም፤ “በዚህ ምርጫ የሚሳፉ ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ ኢትዮጵያን ማገልገል የሚፈልጉ፣ የኢትዮጵያ አንድነት እና ነጻነትን የሚያከብሩ ሁሉም በዚህ ምርጫ ከብልጽግና ያልተናነሰ መልካም እድል እንዲገጥማቸው እመኝላቸዋለሁ” ብለዋል።
“ከብልጽግናም ይሁን ከሌላ ከህዝብ የሚሰርቅ ሌባ አያስፈልገንም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “ከብልጽግናም ይሁን ከሌላ ጠዋት ማታ ሰርቶ የኢትዮጵያን ብልጽግና እና ልማት የማያረጋግጥ አያስፈልገንም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ፤ የአፍሪካ ቀንድን የአፍሪካ ክንድ እናደርጋታለን ሲሉም በመድረኩ የተናገሩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ያዳነው ሀይል የአፍሪካን ቀንድ የአፍሪካ ክንድ ያደርጋታል ሲሉም ተደምጠዋል።