“የምርጫ አስፈጻሚዎች የስልጠና ቁሳቁሶች ስረጭት በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ይጠናቀቃል” ምርጫ ቦርድ
ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የቀሯት ጥቂት ቀናት ናቸው
150ሺ የምርጫ አስፈጻሚዎች በየምርጫ ክልሎች ስልጠና እንደሚወስዱ ቦርዱ አስታውቋል
የምርጫ አስፈጻሚዎች የስልጠና ቁሳቁሶች ስረጭት በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ቁሳቁሶቹ ሳኒታይዘር፣ ማስክ እና በድምፅ መስጫ ቀን አገልግሎት ላይ የሚውሉ እንደ ድምፅ መስጫ ወረቀት እና ፎርሞች መሆናቸውን የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ሶልያና ሽመልስ ገልጸዋል፡፡
የሰልጣኖቹ ቁጥር ከ150ሺ በላይ እንደሆነም ነው የኮሚዩኒኬሽን አማካሪዋ ያስታወቁት፡፡
ቁሳቁሶቹን የማሰራጨት ተግባራት ላለፉት ቀናት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ያስታወሱት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪዋ ሶልያና “ስረጭቱ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል” ብለዋል፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና በየምርጫ ክልል እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡
ወ/ሮ ሶልያና “ለምርጫ አስፈፃሚዎች የሚሰጠው ስልጠና በድምፅ መስጫ ቀን አፈጻጸም፣ የድምጽ ቆጠራ፣ የውጤት አቆጣጠር እና ሌሎች መደረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ተግባራትን የተመለከተ ይዘት ያለው ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
ከጸጥታ ጋር በተያያዘ እስካሁን የገጠመ ችግር እንደሌለ እና የክልል መንግስታት ትብብር ጥሩ የሚባል መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሔድ ቀን የተቆረጠለት መሆኑ ይታወቃል፡፡