ሁለቱ ሀገራት የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በይፋ ስለመጀመራቸው የጋራ መግለጫ ይሰጣሉ
ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመጀመር የእስራኤል ልዑክ ዛሬ ባህሬን ገባ
ዛሬ እሁድ ጥቅምት 08 ቀን 2013ዓ.ም. ሁለተኛው “የሰላም አውሮፕላን” የእስራኤልን እና የአሜሪካን ልዑካን ጭኖ በባህሬን ማናማ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል፡፡ የእስራኤል የሰላም አውሮፕላን ወደ ባህሬን ሲያቀና የመጀመሪያው ሲሆን ከኤምሬቶች ቀጥሎ ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገር ደግሞ ሁለተኛ ጉዞው ነው፡፡
በእስራኤል እና በባህሬን መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በይፋ ለማስጀመር የበረራ ቁጥር El Al “973” ከቴል አቪቭ ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ዛሬ ከሰዓት ነው መናማ አየር ማረፊያ ያረፈው፡፡
“የሰላም አውሮፕላን” በሚል ስያሜ እስራኤል ልዑክ ባለፈው ወር ወደ አቡዳቢ ሲበር ፣ የሚሬትስ ዓለም አቀፍ ኮድ በሆነው “971” የበረራ ቁጥር የተጓዘ ሲሆን በተመሳሳይ ወደ ባህሬንም የሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ኮድ በሆነው “973” የበረራ ቁጥር ነው የተጓዘው፡፡
የእስራኤል እና አሜሪካ ልዑክ ማናማ ሲገባ አንድ ባለስልጣን የያዙት ማስክ
አውሮፕላኑ ከቴል አቪቭ ከተነሳ በኋላ የባህሬን ዋና ከተማ ወደ ሆነችው መናማ አውሮፕላን ማረፊያ ለመድረስ ሁለት ሰዓት ከ ሩብ ፈጅቶበታል፡፡
የእስራኤልን እና የአሜሪካን ልዑካን ባካተተው በዚህ ጉዞ የእስራኤል ልዑክ በሀገሪቱ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሜይር ቤን ሻባት የተመራ ሲሆን የአሜሪካው ልዑክ ደግሞ በሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴፈን ሚኑቺን የተመራ ነው፡፡
በማናማ የእስራኤል እና የባህሬን ባለስልጣናት የተለያዩ ዝርዝር ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል፡፡
እስራኤል እና ባህሬን እ.ኤ.አ. መስከረም 15 በኋይት ሃውስ በተካሔደ ሥነ-ስርዓት “የሰላም ፣ የትብብር እና ገንቢ የዲፕሎማሲ እና የወዳጅነት ግንኙነት” ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ይህ ስምምነት መደበኛ የሚሆንበትን የተለያዩ ዝርዝር ስምምነቶች ተፈራርመው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በይፋ ስለመመስረታቸው የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት የጋራ መግለጫ ይሰጣሉ፡፡
እስራኤልና ዩኤኢም እ.ኤ.አ. መስከረም 15 በኋይት ሃውስ ተመሰሳይ “የአብርሃም ስምምነት” ከተፈራረሙ በኋላ ከወር በፊት የእስራኤል ልዑካን በአቡዳቢ ተገኝተው ሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በይፋ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡