የወታደራዊ መኮንኖች በአምባሳደርነት መሾም ያስነሳውን ጥያቄ ልምድና ብቃትን ያማከለ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተከላከሉ
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ ኢነርጂን መፍጠር እንጅ የዐባይ ውሃን የማቆም አንዳች ፍላጎት የላትምም ብለዋል
የሳውዲ እስረኞች በተመለከትም “የሄደው ሁሉ ህጋዊ አይደለም እናም ተጨማሪ ጥናትና ማጣራት ያስፈልገናል” ብለዋል
የወታደራዊ መኮንኖች በዲፕሎማትነት መሾም ያስነሳውን ጥያቄ በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ስምሪቱ ብቃትና ልምድ መሰረት ያደረገ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በዛሬው እለት ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ለህዝብ እንደራሴዎች በሰጡት ማብራርያ ነው፡፡
የዲፕሎማቶች ስምሪት
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ከዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው በሰጡት ምላሽ የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች አልፋና ኦሜጋ “ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ነው” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በቅርቡ ከተካሄደው የዲፕሎማቶች ስምሪት በተለይም ሀገሪቱ ካለችብት ሁኔታ አንጻር ወታደራዊ መኮንኖችን በአምባሳደርነት መሾም ምን ያክል ተገቢ ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ የተሰጠው የአምባሳደርነት ሹመት “ብቃትና ልምድን መሰረት ያደረገ ነው” እንደሆነ አስረድቷል፡፡
የአምባሳደርነት ምደባ ቅጥር ሳይሆን በፖለቲካ አመራሩ የሚሰጥ ሹመት መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስምሪቱ ለሀገር ጥቅም ተብሎ የተደረገ እንደሆነም አንስቷል፡፡
አሁን ላይ 70 በመቶ የሚሆኑት ዲፕሎማቶች ከውጭ ጉዳይ መመደባቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ መሰል ሹመቶች የፖለቲካ አመራሩ ለሀገር ይጠቅማሉ ብሎ ሲወስን የሚያደርጋቸው የተለመዱ አሰራሮች ናቸውም ብለዋል፡፡
ኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮ-አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ በሰጡት ምለሽ ሁለቱም ሀገራት ታሪካዊ እና የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው አንስቷል፡፡
“አሜሪካውያን በኢትዮጵያ ጥቅም አላቸው እኛም ከአሜሪካ የምናገኘው ጥቅም አለን ፤ ስለዚህም ለጋራ ጥቅማችን ስንል በጋር የምንሰራ ይሆናል”ም ነው ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፡፡
አትዮ-ኤርትራ ግንኙነት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁናዊ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በበርካታ ነገሮች የተጋመዱ ህዝቦች ያልዋቸው ሀገራት መሆናቸው ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የተጀመሩ ትብብሮች ይበልጥ በማጠናከር ሀገራቱ ለጋራና ዘላቂ ጥቅም የሚሰሩ ይሆናል ብለዋል፡፡
የዐባይ ጉዳይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዐባይ ጉዳይ በሰጡት ማብራርያ አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ትልቁ ዓላማ የመልማት መብቷ ማረጋገጥ መሆኑ አስረግጠው ተናግሯል፡፡
ግደቡን በተመለከተ “ኢትዮጵያ ኢነርጂን መፍጠር እንጅ የዐባይ ውሃን የማቆም አንዳች ፍላጎት የላትም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር በተያያዘ የሚነሳው ጉዳይ መፍትሄው በትብብር እና ድርድር ብቻ መሆኑን ግልጽ አድርጓል፡፡
“ሁለቱም ሀገራት ከውሃው የመጠቀም መብት እንዳላቸው ሁሉ ኢትዮጵያም ከውሃው የመጠቀም መብት እንዳላት ሊታወቅ ይገባል”ም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በሳውዲ አረቢያ ስለሚገኙ እስረኞች ጉዳይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳውዲ አረቢያ በመጥፎ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ስለተባሉት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ኢትዮጵያውያን የደህንነት ሁኔታ እና ቀጣይ ስራዎች በሰጡት ምላሸ ሁለቱም መንግስታት ለመፍትሄው በትብብር እየሰሩ መሆናቸው ገልጿል፡፡
በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች ታጉረው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የሳውዲ አረቢያ መንግስት በሀገሪቱ እያካሄደው ካለው የሪፎርም አካል ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ፤ በእስር ከሚገኙ ስደተኞቹ ህጋዊነት እና ስነ-ምግባር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በሳውዲ መንግስት በኩል እንደሚነሱም አልሸሸጉም፡፡
“የሄደው ሁሉ ህጋዊ አይደለም፤ ህጋዊ የሆኑትን ለማወቅ ተቸግረናል እናም ተጨማሪ ጥናትና ማጣራት ያስፈልገናል” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮ-ደቡብ ሱዳን
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የሙርሌ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው በጋምቤላ ክልል የሰነዘሩትን ጥቃት በተመለከተ በሰጡት ማብራርያ፤ መሰል ጥቃቶች በተለያዩ ጊዜያት ሲስተዋሉ የቆዩና መፍትሄ የሚሹ የጋራ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡
ሀገራቱ መሰል ችግር ለመፍታት ወደፊት አብረው የሚሰሩ ይሆናልም ብለዋል፡፡