የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይመን ኮቨነይ በኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ማዘናቸው ገልጸዋል
ኢትዮጵያ አራት የአየርላንድ ዲፕሎማቶችን ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ መወሰኗን ኢትዮጵያ አስታውቃለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት በኢትዮጵያ ይሰሩ የነበሩ አራት የአየርላንድ ዲፕሎማቶች በሳምንት ውስጥ ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑን ገልጸዋል።
የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ባወጣው መግለጫ “ዲፕሎማቶቹ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ከውሳኔ እንደተረሰ እንዳውቅ ተደርጊያለሁ ብሏል።
“ከአምባሳደሩ እና አንድ ዲፕሎማት ውጭ ሌሎች በኤምባሲው ሰራተኞች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የኢትዮጵያ መንግስት በሳምንቱ መጀመርያ አሳውቆኛል” ብሏል ሚኒስቴሩ።
ዲፕሎማቶች ለምን ተባረሩ? ለሚለውም ሚኒስቴሩ በመግለጫው “የኢትዮጵያወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ አየርላንድ የተመድ የጸጥታው ም/ቤትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ መድረክ በበማራምደው አቋም መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አሳውቆኛል” ብሏል።
የአየርላናድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይመን ኮቨነይ በኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ “በኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ በጣም አዝኛለሁ፤ አየርላንድ እንደፈርነጆቹ ከ1994 ጀምሮ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ ነበራት፤ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ጋር በአጋርነት የሀገሪቱን ልማት በመደገፍ ረገድም ስትሰራ ቆይታለች” ብለዋል።
የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ የምናደርገው ተሳትፎ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ/ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬልን ጨምሮ በአውሮፓ ህብረት ከተሰጡት አቋሞች እና መግለጫዎች ጋር ወጥነት ያለው ነው”ም ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአየር ላንድ ኤምባሲ አሁንም ክፍት ሆኖ የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድን ጨምሮ ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነቱን የሚወጣ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ምንም እንኳን የዲፕሎማቲክ ሰራተኞችን ቁጥር በሁለት ሶስተኛ መቀነሱ የኤምባሲው አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ በማቅረቡ ረገድ ተጽእኖ ማሳደሩ የማይቀር ቢሆንም፤ የኤምባሲው ትኩረት የቆንስላ አገልግሎት አቅርቦት ላይ ይሆናልም ብሏል።