ኢትዮጵያን በተለያዩ ሃገራት የወከሉ ዲፕሎማቶች በአዲሱ የውጭ ጉዳይ እና ደህንነት ፖሊሲ ላይ መወያየት ጀመሩ
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ኤምባሲ እና ሚሲዮኖችን ያለ በቂ ጥናት ትከፍት ነበር ተብሏል
ዲፕሎማቶቹ በቀጣዮቹ አስር ቀናት በብሔራዊ ጥቅም እና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ዙሪያ ይወያያሉ ተብሏል
በአዲሱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና ደህንነት ፖሊሲ ላይ ውይይት መካሄድ ተጀመረ።
ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት ወክለው የዲፕሎማሲ ስራዎችን ሲያከናውኑ የቆዩ አምባሳደሮች፣ዲፕሎማቶች እና ሌሎች ባለሙያዎች ወደ አገር ቤት መጥተዋል።
እነዚህ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ባለሙያዎች ለአስር ቀናት በብሔራዊ የውጭ ግንኙነት እና ደህንነት ፖሊሲ ዙሪያ እንደሚወያዩ ተገልጿል።
ምክትል ጠቅላይ ሚሚስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በውይይቱ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
በሱሉልታ ከተማ በሚገኘው የአፍሪካ ስራ አመራር አካዳሚ በሚካሄደው በዚህ ውይይት ላይ ከአዲሱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ እና ደህንነት ፖሊሲ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት በነበሩ የዲፕሎማሲ ስራዎች አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
በኤምባሲዎች፣ሚሲዮኖች ስምሪት እና አደረጃጀት ዙሪያ እንዲሁም ከአዳዲስ የዲፕሎማሲ አሰራሮች አተገባበር ዙሪያ ውይይት ይደረጋልም ብለዋል አቶ ደመቀ።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ስራ በቀጣይ ቴክኖሎጂዎችን በሚገባ መጠቀም በሚያስችል እና ብሔራዊ ጥቅማችንን ያስጠብቃሉ የተባሉ ሁሉንም አሰራሮችን እንደሚከተል አቶ ደመቀ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ተናግረዋል።
አዳዲስ ክስተቶችን እንደ ኮሮና ቫይረስ እና ዲጂታል ዲፕሎማሲን መሰረት ባደረገ መንገድ እንዲሁም ወጭ ቀናሽ የሆኑ የዲፕሎማሲ ስራዎቻችንን እንከተላለን ሲሉም ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ያለ ጥናት እና እቅድ ይከፈቱ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ ከእንግዲህ ግን ሚሲዮኖችን ስንከፍት ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ጥቅም አንጻር፣ ከኢትዮጵያውያን ጋር ያለው ትስስር እና ሌሎች ጥቅሞቻችንን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ይሆናል አምባሳደሮቻችንንም ከዚህ አንጻር ብቻ ተመስርተን እናሰማራለን ብለዋል።
በ2013 ዓመት በዲፕሎማሲው ዓለም ኢትዮጵያ ፈተና ቢበዛባትም ብዙ የዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራታቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ለውጥ ጠሎች እና በሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች አማካኝነት የተፈበረኩ የሐሰት ዘገባዎች፤ በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጠሩ የዲፕሎማሲ ጫናዎች ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደነበሩም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይሁንና በትውልደ ኢትዮጵያውያን ፣በዲፕሎማቶቻችን ጥረት፣ በኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ድጋፍ እና በዲጅታል ዲፕሎማሲ ሰራዊቶቻችን አማካኝነት ጫናውን መቋቋም መቻሉንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በቀጣዮቹ አስር ቀናት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የአገር ፍላጎትን መሰረት ያደረገ እና አለም አቀፍ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ለዲፕሎማሲ ባለሙያዎቹ እንደሚሰጥ የፕሮግራሙ መርሀግብር ያስረዳል።