አሜሪካ ከኢራን የጦር መሳሪያ እና የኑክሌር መርሀ ግብር ጋር ግንኙነት በላቸው አካላት ላይ ማዕቀብ ልትጥል ነው
በኢራን ላይ በተባበሩት መንግስታት ተጥሎ ሊያበቃ የተቃረበው ማዕቀብ እንዲቀጥልም አሜሪካ ወስናለች
የአሜሪካ የተናጥል ዉሳኔ በሀገሪቱ ወዳጅ ሀገራትም ጭምር አልተወደደም
አሜሪካ ከኢራን የጦር መሳሪያ እና የኑክሌር መርሀ ግብር ጋር ግንኙነት በላቸው አካላት ላይ ማዕቀብ ልትጥል ነው
አሜሪካ በኢራን የኑክሌር ፣ ሚሳዬል እና በተለመዱት የጦር መሳሪያዎች መርሃ ግብሮች ላይ የተሳተፉትን ከሃያ በላይ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ተናገሩ፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉጉት ባለሥልጣኑ ኢራን በዓመቱ መጨረሻ ለኑክሌር መሳሪያ የሚውል በቂ ቁሳቁስ ሊኖራት እንደሚችል እና ቴህራን ኒውክሌር ከታጠቀችው ሰሜን ኮሪያ ጋር የረጅም ርቀት ሚሳኤል ትብብር እንደጀመረች ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ሁለቱንም ማረጋገጫዎች በተመለከተ ዝርዝር ማስረጃ አላቀረቡም፡፡
የኢራን ወታደሮች በባህረ ሰላጤው የሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ በልምምድ ላይ
አዲሱ ማዕቀብ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን አካባቢያዊ ተፅእኖ ለመገደብ ከሚያደርጉት ጥረት ጋር የሚስማማ ሲሆን በአሜሪካ አደራዳሪነት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ባህሬን ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን መደበኛ ለማድረግ ከተስማሙ ከአንድ ሳምንት በኋላ ይፋ የሆነ ነው፡፡
ይህ አዲስ ማዕቀብ አሜሪካ በኢራን ላይ የተጣለው የተባበሩት መንግስታት ማዕቀብ እንዲቀጥል መወሰኗን ያልደገፉ የአውሮፓ አጋሮቿ ፣ ቻይና እና ሩሲያም የተለያዩ ኩባንያዎቻቸው ከኢራን የጦር መሳሪያ መርሀ ግብሮች ጋር ግንኙነት ካላቸው ፣የማዕቀብ ሰለባ እንደሚሆኑ በማሰብ ዝንባሌያቸውን እንዲያጤኑ ለማስገንዘብ ያለመ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የኢራን ወታደሮች በባህረ ሰላጤው የሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ በልምምድ ላይ
የዓለም ኃያላን እና ኢራን በ2015 (እ.ኤ.አ) የደረሱትን የኑክሌር ስምምነት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በ2018 አሜሪካን ከስምምነቱ ዉጭ አድርገዋል፡፡ ይህ የፕሬዝዳንቱ ዉሳኔ በአውሮፓ ሀገራት እንዲሁም በቻይና እና ሩሲያ ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡
ከዚህ በኋላ ኢራንም የኑክሌር መርሀ ግብሯን የቀጠለች ሲሆን ይህ ያልተዋጠላት አሜሪካ በቅርቡ የሚያበቃው ከወዳጆቿም ይሁን ከባለአንጣ ሀገራት በተለየ የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ እንዲቀጥል ከመፈረም ባለፈ ተጨማሪ ማዕቀቦችንም ለመጣል አቅዳለች፡፡
የአሜሪካ እርምጃ ኢራንን አንደማያሳስባት የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ በሰጡት አስተያየት የገለጹ ሲሆን ሀገራቸው የራሷን አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ስለመናገራቸው ዘ ናሺናል በትናንትናው ዕለት ዘግቧል፡፡