በ5 ዓመት ውስጥ 107 ደቂቃዎች ብቻ ተጫውቶ 11 ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለው ተጫዋች
ስኮት ካርሰን የተባለው የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋች በ5 የውድድር ዘመን ውስጥ 2 ጊዜ ብቻ ሜዳ ገብቷል
ማንቸስተር ሲቲ የ2023/24 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወቃል
የማንቸስተር ሲቲው ተጫዋች ስኮት ካርሰን በ5 ዓመት ውስጥ 107 ደቂቃዎች ብቻ ተጫውቶ 11 ዋንጫዎችን ማንሳት መቻሉ ተነግሯል።
ስኮት ካርሰን የማንቸስተር ሲቲ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ሲሆን፤ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በቆየበት 5 የውድድር ዘመን ወደ ሜዳ ገብቶ የተጫወተው በ2 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነው ተብሏል።
ግብ ጠባቂው ስኮት ካርሰን በሲቲ ቆይታው በ5 የውድድር ዘመን እስካሁን የተጫወተው በአጠቃላይ ለ107 ደቂቃዎች ብቻ ሲሆን፤ ከከልቡ ጋር በመሆን ግን 11 ዋጫዎችን አንስቷል።
ካርሰን ወደ ሲቲ ከመምጣቱ በፊት በቻምፒየንስ ሺፕ ውስጥ ለሚገኘው ደርቢ ካውንቲ ሲጫወት የነበረ ሲሆን፤ በደርቢ ካውንቲ ቆይታውም ከ170 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል።
ተጫዋቹ ከደርቢ ካውንቲ በፊትም እዛው ቻምፒየንስ ሺፕ ውስጥ ለሚገኘው ዊጋን አትሌቲክስም ሲጫወት እንደበረ ማህደሩ ያመለክታል።
በእንግሊዟ ዋይትሄቨን የተወለደው ስኮት ካርሰን ለበርካታ የእንግሊዝ ክለቦች ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ጨዋታውን ማድረግ የጀመረውም በሊድስ ዩናትድ እንደሆነም ተነግሯል።
በመቀጠልም ወደ ሊቨርፑል ያቀና ሲሆን፤ በሊቨርፑል ቆይታውም በሁለት የውድድር ዘመን ቆይታው 9 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነው ተሰልፎ የተጫወተው።
ዌስትብሮምዊች አልቢዮን የቋሚ ተጫዋችነት ስፍራን ከማግኘቱ በፊትም በሼፊልድ፣ ቻርልተን አትሌቲክስ እና አስቶንቪላ ከዚያም በቱርክ ውስጥ ከቡርስስፖ ጋር ተጫውቷል።
ስኮት ካርሰን ማነቸስተር ሲቲን የተቀላቀለው በፈረንጆቹ 2019 ሲሆን፤ ወደ ሜዳ ገብቶ የተጫወተው ግን በ2020/21 እና በ2021/22 የውድድር ዘመን በሁለት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነው ተብሏል።
ሆኖም ግን በእያንዳንዱ ሲቲ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ በመገኘት ከክለቡ ጋር 11 ዋንጫዎችን ያነሳ ሲሆን፤ 11 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችሏል።
ማንቸስተር ሲቲ የ2023/24 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ሻምፒዮን መሆኑ ያታወቃል።