ኢራናውያን ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች የመመረዝ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው ተባለ
በሁኔታው የተደናገጡት አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት እንዲወስዱ መገደዳቸውም ነው የተገለጸው
ጥቃት ፈጻሚዎቹ የሴቶችን ትምህርት የሚቃወሙ አክራሪ የሃይማኖት ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል
በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ገበታ በሚውሉ ኢራናውያን ልጃገረዶች ላይ የመመረዝ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ከቅርብ ወራት ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን ልጃገረዶች የመመረዝ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡
ጥቃት ፈጻሚዎቹ የሴቶችን ትምህርት የሚቃወሙ የሃይማኖት ቡድኖች ሊሆኑ እንሚችሉም ነው የሀገሪቱ ፖለቲከኞች የገለጹት፡፡
የጤና ጥበቃ ምክትል ሚኒስትር ዩኔስ ፓናሂ "አንዳንድ ሰዎች ትምህርት ቤቶች በተለይም የሴቶች ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ እንደሚፈልጉ ተደርሶበታል" ማለታቸው የኢራን የዜና ወኪል ዘግቧል።
ጥቃቱ የተፈጸመው የ22 ዓመቷ ኢራናዊት ኩርድ ማህሳ ጸጉርሽን በትክክል አልሸፈንሽም በሚል በቴህራን የደንብ አስከባሪ ፖሊሶች መገደሏን ተክተሎ በኢራን መሪዎች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እየተንጸባረቀ ባለበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል ተብሏል፡፡
የመርዙ ጥቃት የተፈጸመው የሺዓ ሙስሊም ቅዱስ ከተማ ኩምን ጨምሮ ቢያንስ በአራት ከተሞች በሚገኙ ከ30 በላይ ትምህርት ቤቶች መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሁኔታው የተደናገጡት አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት እንዲወስዱ ተገደዋልም ነው የተባለው፡፡
አንዳንድ በሆስፒታል ተኝተው የሚገኙ ልጃገረዶች ከተመረዙ በኋላ የማቅለሽለሽ ስሜት እንደተሰማቸው እና የልብ ምታቸው መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
በቦሩጅርድ ከተማ በሚገኘው የወንዶች ትምህርት ቤት አንድ ወንድ ኢላማ መደረጉን የመንግስት ሚዲያ ዘግቧል።
የህግ ባለሙያ አሊሬዛ ሞናዲ እንዳሉት ልጃገረዶች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚከለክለው “የዲያብሎስ ፍላጎት” መኖሩ ከባድ ስጋት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ባለሙያው “የዲያብሎስ ፍላጎት” ሊኖራቸው ስለሚችሉ አካላት ያሉት ነገር ባይኖርም፤ ትችታቸው ያነጣጠረው ራሳቸውን የእስልምና ጠባቂ አድርገው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ላይ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል፡፡
ሁን በኢራናውያን ሴቶች ላይ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት እንደፈረንጆቹ በ 2014 በኢስፋሃን ከተማ ጎዳናዎች ላይ ከባድ የአሲድ ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ የተደረገና የአለባበስ ስርዓት የጣሱ ሴቶችን ለማሸበር ያለመ ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡