ከ300 በላይ ሰዎች የተገደሉበት የኢራን ሁኔታ “አስጨናቂ” ነው ሲሉ የተመድ የመብቶች ሃላፊ ተናገሩ
የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ በስነ-ምግባር ፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለች ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ተቃውሞ ተቀስቅሷል
እስካሁን በኢራን ከ31 ግዛቶች ውስጥ በ25ቱ ግዛቶች ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር በኢራን ያለው ሁኔታ "አስጨናቂ" ነው ሲሉ ባለሥልጣናቱ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከ300 በላይ ሰዎች ለሞቱት ተቃውሞ የሰጡት ምላሽ እየጠነከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
የተመድ የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ቱርክ “በኢራን በተደረጉ ተቃውሞዎች የሚገደሉ ሰዎች ህጻናትን ጨምሮ ቁጥሩ እየጨመረ፤ የጸጥታ ኃይሎች ምላሽም መጠናከር የሀገሪቱን አሳሳቢ ሁኔታ ያመለክታሉ” ብለዋል።
በወርሃ መስከረም የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ “ተገቢ ያልሆነ ልብስ” ለብሳለች በሚል በስነ-ምግባር ፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለች ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ኢራን በፈረንጆቹ ከ1979 አብዮት ወዲህ ከነበሩት ፈተናዎች መካከል አንዱ ነው የተባለውና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ወደ ህዝባዊ አመጽነት የቀየረውን ተቃውሞ በማቀነባበር የውጭ ጠላቶችን እና ወኪሎቻቸውን ወቅሳለች።
የኢራን የዓለም ዋንጫ ቡድን የሀገሪቱን መዝሙር ለመዘመር ፈቃደኛ አለመሆንም የአመጹን ከፍታ አሳይቷል ነው የተባለው።
የተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ፅህፈት ቤት እንዳስታወቀው እስካሁን ከ40 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል። ሮይተርስ እንደዘገበው ከሀገሪቱ ከ31 አውራጃዎች በ25ቱ ሰዎች ሞተዋል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጄረሚ ላውረንስ ባለፈው ሳምንት ከ40 በላይ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን በመጥቀስ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢራን መንግስት መገናኛ ብዙኸን ባለፈው ወር እንደዘገበው በተቃውሞ ሰልፉ ፖሊስን ጨምሮ ከ46 በላይ የጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል።