ፖላንድ ሁሉም ወንድ ዜጎቿ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ የሚያደርግ ዕቅድ አስተዋወቀች
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እቅዱ የፖላንድን ወታደራዊ አቅም ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ለፓርላማው ተናግረዋል

ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ 4.7 በመቶ የሚሆነውን ለመከላከያዋ የበጀተችው ፖላንድ ከአሜሪካ ጋር የ20 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት ፈጽማለች
ፖላንድ ሁሉም ወንድ ዜጎቿ በወታደራዊ ስልጠና ውስጥ እንዲያልፉ የሚያስችል ረቂቅ ህግ ለፓርላማው አቀረበች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ረቂቅ ህጉን ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ስልጠና እንዲሰጥ ያስችላል የተባለው ዕቅድ ዝርዝር በመጪዎቹ ወራት ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
“በፖላንድ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ጎልማሳ ወንድ በጦርነት ጊዜ ሀገሩን እና ቤተሰቡን ከጥቃት መከላከል የሚችልበትን የስልጠና ቅርጽ እያዘጋጀን ነው፤ እቅዱ በሀገሪቱ ሊፈጠሩ ለሚችሉ አደጋዎች ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ይፈጥርልናል” ብለዋል፡፡
በእቅዱ መሰረት ወታደራዊ ስልጠና የሚያገኙት ወንዶች በቀጥታ መከላከያ ሰራዊቱን የሚቀላቀሉ ሳይሆኑ በግጭት ወቅት ብቁ ወታደራዊ ቁመና ተላብሰው መሰለፍ የሚችሉበትን ክህሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የተያዘው እቅድ ለሴቶችም ስልጠና የመስጠት ሀሳብ እንዳለው ለአሁኑ ግን ትኩረቱን ወንዶች ላይ ማድረጉ ተብራርቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 200 ሺህ ወታደሮች ያሏት ፖላንድ በአቅራቢዋ ከሚገኙ ሀገራት አንጻር ያላት የሰራዊት ቁጥር አነስተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
1.3 ሚሊየን ሰራዊት ያለት ሩስያን እና 800 ሺህ ወታደሮች ያሏት ዩክሬንን ለንጽጽር ያነሱት ዶናልድ ተስክ ሀገራቸው የወታደር ቁጥሯን ከ200 ሺህ ወደ 500 ሺህ ማሳደግ እንደሚኖርባት አሳስበዋል፡፡
“እያሰብን ያለነው ፖላንድ ተጠባባቂ ጦርን ጨምሮ 500 ሺህ ወታደሮች እንዲኖራት ነው ይህም አሁን በአውሮፓ እየታየ ካለው የደህንነት ስጋት አኳያ እያደገ ሊሄድ የሚገባው ነው” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ፈረንሣይ አውሮፓን በኒውክሌር ጥላ ስር ለማካተት ያቀረበችውን ሀሳብ መንግሥታቸው በጥንቃቄ እየመረመረው ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ፖላንድ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ 4.7 በመቶ የሚሆነውን ለመከላከያዋ በመበጀት ከኔቶ አባል ሀገራት መካከል ከፍተኛውን ወታደራዊ ወጪ ለማውጣት እቅድ ይዛለች፡፡
ከዚህ ባለፈም አሜሪካ ሰራሹን 250 ኤም1ኤ2 አብርሀም ታንክ ፣ 32 ኤፍ 35 የውጊያ ጄቶችን ፣ ሚሳኤል እና የተለያዩ ሄሊኮፕተሮችን ለመግዛት ከአሜሪካ ጋር የ20 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት ፈጽማለች፡፡