ትራምፕ በሩሲያ ላይ "መጠነ ሰፊ" ማዕቀብ እና ታሪፍ ለመጣል ዛቱ
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱን ለማስቆም "ሳይረፍድባቸው" ስምምነት ላይ እንዲደርሱም አሳስበዋል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከሰሞኑ ለኬቭ የሚደረግ ወታደራዊ ድጋፍን ማቋረጣቸው የሚታወስ ነው
አሜሪካ በሩሲያ ላይ "መጠነ ሰፊ" ማዕቀብና ታሪፍ ልትጥል እንደምትችል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
ከቀናት በፊት ለዩክሬን የሚደረግ ወታደራዊ ድጋፍ እና የደህንነት መረጃን ማጋራት ያቋረጡት ፕሬዝዳንቱ ሁለቱም ተፋላሚ ሀገራት ወደ ድርድር እንዲገቡ አሳስበዋል።
ዋይትሃውስ ከሩሲያ ጋር ግንኙነቱን ለማደስ የተወሰኑ ማዕቀቦችን ለማንሳት እየተዘጋጀ መሆኑን ሬውተርስ ባለፈው ሰኞ ምንጮቹን ጠቅሶ ቢዘግብም ትራምፕ ትናንት በትሩዝ ሶሻል ማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በሞስኮ የባንክ ስርአት ላይ ማዕቀብ ሊጣል እንደሚችል አመላክተዋል።
"ሩሲያ በአውደ ውጊያ ዩክሬንን እያወደመች ነው፤ በመሆኑም የተኩስ አቁም አልያም ዘላቂ የሰላም ስምምነት እስኪፈረም ድረስ በሩሲያ ባንኮች ላይ መጠነ ሰፊ ማዕቀብ ለመጣል አስቤያለሁ፤ ታሪፍም ሊኖር ይችላል" ብለዋል ትራምፕ በመልዕክታቸው።
"ሩሲያ እና ዩክሬን ሳይረፍድባቸው አሁኑኑ ወደ ጠረጼዛ ዙሪያ ንግግር መግባት አለባቸው" ሲሉም አክለዋል።
ለሶስት አመቱ ጦርነት ዩክሬንን ተጠያቂ የሚያደርጉት ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ ከተመለሱ በኋላ በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ትችት ሲያሰሙ አልተደመጡም። ፑቲን የሰላም ስምምነት እንዲደረስ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ከሞስኮ ጋር ግንኙነታቸውን ለማደስ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።
በአንጻሩ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት በቃላት ከመወረፍ ተሻግረው ለኬቭ የሚደረግ ወታደራዊ ድጋፍን አቋርጠዋል።
ዩክሬን ባለፉት ሶስት ቀናት ወደ ሩሲያ ኩርስክ ክልል ያስገባቻቸው ወታደሮች በሩሲያ ከባድ የመልሶ ማጥቃት እየተፈጸመባቸው በከበባ ውስጥ እንደሚገኙ ሬውተርስ ዘግቧል።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በሚደረግ የሰላም ስምምነት ንግግር እንደ መደራደሪያ ልትጠቀምበት ያሰበችው ኩርክስ ክልል በቅርቡ ከእጇ ሊወጣ እንደሚችልም እየተነገረ ነው።
ከነጩ ቤተመንግስት ዱላ ቀረሽ ንትረክ በኋላ የአውሮፓውያኑን ድጋፍ ለማግኘት ወደ ለንደን እና ብራሰልስ ያቀኑት ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ከነገ በስቲያ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ያቀናሉ። ልኡካቸውም በሪያድ አልያም በጂዳ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
በሳኡዲው ምክክር መሻከር የታየበትን የዋሽንግተን እና ኬቭ ግንኙነት ለማደስ ስምምነት ይደረሳል ብለው እንደሚጠብቁ የዋይትሃውስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልዝ ተናግረዋል።
የዩክሬንን ከ20 በመቶ በላይ መሬት የተቆጣጠረችው ሩሲያ በብሪታንያ እና ፈረንሳይ የቀረበውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እና የአውሮፓ ሀገራት ወታደሮችን በሰላም አስከባሪነት የማሰማራት ሃሳብ እንደማትቀበለው ማስታወቋ የሚታወስ ነው።