“አርሰናል ለአርቴታ የሰጠውን ጊዜ ያህል ማንችሰተር ዩናይትድ ለእኔ አይሰጠኝም” - ሩብን አሞሪም
የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩብን አሞሪም አርቴታ አርሰናልን የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን አድርጎ የሰራበትን ጊዜ ያህል ከዩናይትድ እንደማያገኙ ተናግረዋል

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በነገው ዕለት መድፈኞቹ ወደ ኦልትራፎርድ ተጉዘው ቀያይ ሰይጣኖቹን ይገጥማሉ
በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ፖርቹጋላዊው የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩብን አሞሪም በኦልትራፎርድ ሰፊ የጊዜ እድል እንደማይሰጠው ተናግሯል፡፡
አሞሪም ሚኬል አርቴታ በአርሰናል ቤት የተለያዩ ለውጦችን እንዲያደርግ የተሰጠውን ጊዜ እንደማይሰጠው ነው የገለጸው፡፡
"አርቴታ የተሰጠው ጊዜ አይኖረኝም ሆኖም አርቴታ በአርሰናል ቤት በነበረበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በርካታ ጉዳዮችን ካስተካከለበት መንገድ የምማረው ነገር ይኖራል” ሲል ተናግሯል፡፡
ከቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ የከፋ አፈጻጸም እያስመዘገበ ነው በሚል በእንግሊዝ ጋዜጦች እና በስፖርቱ ቤተሰቦች እየተተቸ የሚገኘው አሞሪም ጫናው በርትቶበታል፡፡
በሩብን አሞሪም ስር ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ዩናይትድ ከኤፍኤ ዋንጫ ፉክክር ውጭ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም ቡድኑ ለመጨረሻ በሜዳው ጊዜ ካደረጋቸው 7 ግጥሚያዎች ሁለቱን ብቻ በማሸነፍ በ”ትያትር ኦፍ ድሪምስ” ጥቁር ታሪክ ጽፏል፡፡
ስፔናዊው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በታህሳስ 2019 ኡናይ ኤምሪን በመተካት ሀላፊነቱን ከተረከበ በኋላ መድፈኞቹ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን እንዲሆኑ አድርጎ መስራት ችሏል፡፡
አሰልጣኙ ወደ ኤምሬትስ ከመጣ በኋላ በመጀመሪያው የውድድር ዘመን የ2020 ኤፍኤ ዋንጫን ማሸነፍ ቢችልም ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ያሸነፈው ብቸኛው ዋንጫ ሆኖ ቀጥሏል፤ ከዚህ ባለፈም ክለቡን ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ተፎካካሪነት ለመመለስ ሶስት የውድድር ዘመናት ፈጅቶበታል።
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በነገው ዕለት መድፈኞቹ ወደ ኦልትራፎርድ ተጉዘው ቀያይ ሰይጣኖቹን ይገጥማሉ፡፡
ዩናይትድ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ፣ ሉክ ሻው እና ሜሰን ማውንትን ጨምሮ በርካታ ቁልፍ ተጨዋቾች ሳይዝ መድፈኞቹን ይገጥማል፡፡
አሞሪም በእሁድ ምሽቱ ጨዋታ ሌሎች የተጎዱ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ እንደማይመለሱ ተናግሮ በአሰልጣኙ ስር ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳየ የነበረው አማድ ዲያሎ የውድድር ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት ቡድኑን ሊቀላቀል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡
ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ኮቢ ማይኖ ፣ ሃሪ ማጉየር፣ ማኑዌል ኡጋርቴ ፣ ሜሰን ማውንት እና ሉክ ሻው የውድድር ዘመኑ ከማለቁ በፊት ወደ ሜዳ ይመለሳሉ ተብለው የሚጠበቁ ሌሎች ተጫዋቾች መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ አርሰናል ፒኤስቪን 7-1 ሲያሸንፍ ዩናይትድ ከሁለት ቀናት በኋላ ከሪያል ሶሲዳድ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡
አርሰናል በሊጉ ታሪክ በማችስተር ዩናይትድ የተሸነፈውን ያህል በሌላ ክለብ ተሸንፎ አያውቅም፤ ቀያይ ሰይጣኖቹ መድፈኞችን 99 ጊዜ ሲያሸንፉ ከአርሰናል በላይ 106 ጨወታዎችን ያሸነፉት አስቶንቪላን ነው፡፡
ሚኬል አርቴታ አርሰናልን በአሰልጣኝነት እየመራ 200ኛው የሊግ ጨዋታውን ነገ የሚያደርግ ሲሆን ከዩናይትድ ጋር ካደረጋቸው 10 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሰባቱን አሸንፏል።
በተጨማሪም በሊጉ ቢያንስ አምስት ጊዜ ዩናይትድን ከሚገጥሙት አሰልጣኞች መካከል አርቴታ 70 በመቶ የማሸነፍ እድል አለው።