ዶናልድ ትራፕምን ለመግደል የዛተው ሰው ተያዘ
የአሜሪካ እጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሪዞና የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ እንደሚገድል የዛተው ሰው በፖሊስ መታሰሩ ተገልጿል
የ66 ዓመቱ ሮናልድ ሊ በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ላይ የግድያ ዛቻውን ካሰራጨ በኋላ ሊታሰር ችሏል
ዶናልድ ትራፕምን ለመግደል የዛተው ሰው ተያዘ፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር በሆነችው አሜሪካ የፊታችን ሕዳር ወር ላይ ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር አቅራቢያ ባለችው አሪዞና የምርጫ ቅስቀሳ ነበራቸው፡፡
ሮናልድ ሊ የተሰኘው የዚሁ ግዛት ነዋሪ ዶናልድ ትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ሲያደርጉ እንደሚገድላቸው በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ላይ የዛቻ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ቅስቀሳቸውን እያደረጉ እያለ ፖሊስ ይሄንን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር እንዳዋለው ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የግድያ ዛቻ ያደረገ ሰው ስለመያዙ እንዳልሰሙ የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው “ምንም የሰማሁት ነገር አልነበረም” ብለዋል፡፡
ብሰማም የሚለወጥ ነገር አይኖርም ነበር ያሉት ትራምፕ ለተፈጠረው ክስተት ካማላ ሀሪስን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ምርጫ ካሸነፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን እንደሚያባርሩ ተገለጸ
የእነ ካማላ ሀሪስ አስተዳድር ነው ህገወጥ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዲገባ ያደረገው ያሉት ትራምፕ “እኔ ለህገወጥ ስደተኞች መጥፎ ሰው ነኝ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕን እንደሚገድል መዛቱን ተከትሎ በፖሊስ የተያዘው ተጠርጣሪው ከዚህ በፊት በብዙ ወንጀሎች ይፈለግ የነበረ ሰው እንደነበር በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከአንድ ወር በፊት በፊላዴልፊያ ግዛት የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ እያሉ ከግድያ ሙከራ ለጥቂት መትረፋቸው አይዘነጋም፡፡
የደህንነት ሀይሎች ወደ ዶናልድ ትራምፕ የተኮሰው እና ያቆሰለውን ተጠርጣሪ ወዲያውኑ መግደላቸውም ይታወሳል፡፡