መንግስት ተቃውሞ የበረታበትን አዲስ የፋይናንስ ህግ ተፈጻሚ እንደማያደርግ ቢያሳውቅም ፕሬዝዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ድምጾች በርትተዋል
በኬንያ ከሰሞኑ ከታክስ ጭማሪ ጋር በተገናኘ የወጣው የፋይናንስ ህግ የቀሰቀሰው ተቃውሞ አሁንም እንዳልበረደ ተሰምቷል፡፡
የ23 ሰዎች ህይወትን የቀጠፈውን ተቃውሞ ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሀገሪቱ ፓርላማ ከትላንት በስቲያ በጸደቀው ህግ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ ተናግረዋል።
የታክስ ጭማሪን ተግባራዊ ያደርጋል የተባለውና ኬንያ የውጭ እዳዋን ለመቀነስ የምታውለውን 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ያስገኛል የተባለው የፋይናንስ ህግ ውድቅ ቢደረግም አሁንም የህዝብ መሰባሰቦች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስተዋሉ ይገኛሉ፡፡
በዋና ከተማዋ ናይሮቢ እና በሞምባሳ የተሰባሰቡ ሰልፈኞች በቀጣዮቹ ቀናት የፕሬዝዳንቱን ከስልጣን መውረድ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ እየተዘጋጁ ነው ተብሏል፡፡
ፖሊስ በናይሮቢ ለተቃውሞ የተሰባሰቡ ሰዎችን ለመበተን ባደረገው ጥረት ከሰልፈኞች ጋር የተጋጨ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ ቤተ መንግስት የሚወስዱ መንገዶች መዘጋታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
በትላንትናው እለት የፋይናንስ ህጉ እንደማይጸድቅ ቢነገርም የተለያዩ የፖለቲካ የማህበረሰብ አንቂዎች በሀገሪቱ መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል በሚል ተቃውሞው እንዲቀጥል በማህበራዊ ትስስር ገጽ ጥሪ እያቀረቡ ነው፡፡
ዛሬን ጨምሮ በቀጣዮቹ ቀናት የታቀዱት የተቃውሞ ሰልፎች እንዲቆሙ የጠየቁት የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻጉዋ ወጣቶች ለውይይት እድል እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
መሪ የለውም በተባለው ተቃውሞ በአሁኑ ወቅት በሰልፈኞቹ መካከል የተለያዩ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ሲሆን አንዳንዶች የታክስ ህጉ የማይተገበር ከሆነ ሰላማዊ ሰልፉ እንዳማያስፈልግ ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን ለቀው አዲስ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ተቃውሞው መቀጠል አለበት እያሉ ይገኛሉ፡፡
በነዚህ ሀሳቦች ጎራ ያሉ የፖለቲካ አንቂዎችም በተመሳሳይ በሀሳብ ልዩነት እየተሟገቱ ሲሆን ሰልፉ መቀጠል የለበትም የሚለውን ሀሳብ የሚያቀነቅኑት ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሰልፉ የሚቀጥል ከሆነ በየትኛውም አማራጭ ለማስቆም እንገደዳለን ሲሉ የገለጹትን ዛቻ በማንሳት ተጨማሪ የወጣቶችን ሞት ለማስቀረት ሰልፉ እንዲቀር ጠይቀዋል።
የሰልፉን መቀጠል የሚሹ የፖለቲካ አንቂዎች ደግሞ በሀገሪቱ ያለውን የሰራ አጥ ቁጥር እና የኑሮ ውድነት በመጥቀስ መሰረታዊ የመንግስት ለውጥ ስለሚያስፈልግ ተቃውሞው መቀጠል አለበት እያሉ ነው።
የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመጹን ሊያባብስ ይችላል በሚል መከላከያ ሰራዊቱ በከተማዋ እንዳይሰማራ ቢከለክልም በዛሬው እለት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች በዋና ከተማዋ በተሸከርካሪ ላይ ቅኝት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዋና ከተማዋ ናይሮቢ እና ሞምባሳን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፖሊስ እና ወታደር ተሰማርቶ እንደሚገኝ የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡