በኬንያ በእባብ ተነድፈው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተነገረ
በሀገሪቱ በአመት በእባብ ከሚነደፉ 20ሺህ ሰዎች 4ሺህ ያክሉ ህይወታቸው ያልፋል
ለመርዙ ማርከሻ የሚሰጠው ክትባት ውድ መሆን የብዙዎችን ህይወት እያስከፈለ ነው ተብሏል
በኬንያ በየአመቱ በእባብ ተነድፈው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በመጨመር ላይ እንደሚገኝ ተነገረ፡፡ በሀገሪቱ በየአመቱ በእባብ ከሚነደፉ 20ሺህ ሰዎች 4ሺህ ያህሉ ህይወታቸው ሲያልፍ 7ሺዎቹ ደግሞ ፓራላይዝድ ይሆናሉ ተብሏል።
የጫካ ምንጠራ እና የአየርን ንብረት ለውጥ የፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት እባቦች ውሀ እና ምግብ ፍለጋ ወደ ሰዎች መኖርያቤቶች እንዲመጡ አድርጓል ብሏል የሀገሪቱ ጤና ቢሮ።
በዚህ ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ እየጨመረ እንደሚገኝ ገልጿል።
ከሊቨርፖል ስኩል ኦፍ ትሮፒካል ሜድስን ጋር በጋራ እየሰራ የሚገኝው የኬንያ የእባብ ጸረ መርዝ ክትባት ምርምር ተቋም ሃላፊ ጆፍሪ ማራኛ በሀገር ውስጥ ክትባቱን የሚያመርቱ ኩባንያዎች ባለመኖራቸው በእባብ ለተነደፉ ሰዎች የሚሰጠው ህክምና ዋጋ ወድ እንዲሆን እንዳደረገው ይናገራል።
በዚህ የተነሳም በእባብ ከሚነደፉ ኬንያውያን መካከል ግማሹ ወደ ህክምና ተቋማት አይሄዱም።
በአሁኑ ወቅት አንድ ክትባት ለማግኝት እስከ 300 ዶላር ድረስ ተጎጂውን ሊያስወጣ እንደሚችል የሚያነሳው ሃላፊው ፤ ተጠቂዎቹ ከደሀ የገጠር መንደሮች የሚመጡ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ የሚኖሩ መሆናቸው እና ህክምናውን ለማግኘት አቆራርጠው የሚመጡት መንገድ መርዘም የጉዳት መጠኑን እያከፋው ይገኛል ብሏል።
ኬንያ ከሜክሲኮ እና ህንድ የምታስገባቸው ጸረ የእባብ መርዝ ክትባቶች በሀገሪቱ ካሉ የእባብ ዝርያዎች ጋር የማይጣጣሙ በመሆናቸው ሙሉ ለሙሉ የማይፈውሱበት አጋጣሚ አለ።
በመሆኑም የሀገሪቱ ምርምር ተቋም ይህን ችግር ለመቅረፍ ብላክ ማምባ ከተባለው የእባብ ዝርያ መርዝ በመሰብሰብ ክትባቶችን ለማምረት ጥረት እያደረገ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት አመታት አስተማማኝ ውጤት ላይ ለመድረስ አስቦ እየሰራ ነው።
ናይሮቢ በሀገሪቷ እየጨመረ የሚገኝውን በእባብ የሚነደፊ ሰዎችን ሞት ለመቀነስ በአመት 100ሺ ዶዝ ክትባት ያስፈልጋታል።
በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ 5.4 ሚሊየን ሰዎች በእባብ የሚነደፉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ137 ሺህ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው ያልፋል።