አውሮፕላን ውስጥ "ግርግርና ወከባ" ፈጥረዋል ባላቸው ግለሰቦች ላይ ምርመራ መጀመሩን ፓሊስ አስታወቀ
ፖሊስ እንዳስታወቀው ግለሰቦቹ "ግርግርና ወከባ" የፈጠሩት ከቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ መቀሌ ለመጓዝ በተዘጋጄ አውሮፕላን ውስጥ ነው
የፌደራል ፖሊስ የአቬሽን ህግና አሰራርን ጥሰዋል ያላቸውን ስድስት ግለሰቦች ሽብር በመፍጠር ጠርጥሮ ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን አስታወቀ
የፌደራል ፖሊስ በአዲስ አበባ ቦሌ አየርመንገድ የአቬሽን ህግና አሰራርን ጥሰዋል ያላቸውን ስድስት ግለሰቦች ሽብር በመፍጠር ጠርጥሮ ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን አስታወቀ።
የፌደራል ፖሊስ በፌስቡክ ገጹ እንዳስታወቀው ግለሰቦቹ "ግርግርና ወከባ" የፈጠሩት ከቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ መቀሌ ለመጓዝ በተዘጋጄ አውሮፕላን ውስጥ ነው።
ፓሊስ ምርመራ እያካሄደባቸው ያሉት ተጠርጣሪዎች ዮሀንስ ዳንኤል፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤሊያስ ድሪባ እና ይዲድያ ነጻነት ናቸው።
ከቀናት በፊት ተሳፋሪ በነበሩት ግለሰቦች እና በአየርመንገዱ የደህንነት ሰዎች መካከል የተፈጠረውን እሰጣገባ የሚያሳዩ ቪዲዮች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወሩ ታይተዋል።
በቪዲዮው ውስጥ እነዚህ ግለሰቦች ከአውሮፕላኑ "አንወርድም" ሲሉ እና የደህንነት ሰራተኞቹ ደግሞ "ወረዱ" መሄድ አይቻልም እያሉ ሲጨቃጨቁ ተደምጠዋል።
ግለሰቦቹን ከጸረ-ሰላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ጭምር እንደጠረጠራቸው የገለጸው ፖሊስ ድርጊቱ በተፈጸመበት ወቅት የደህንነት ኃይሎች እና የበረራ ባለሙያዎች ሁኔታውን ለማርገብ ቢማጸኗቸውም ሳይሰሟቸው ቀርዋል ብሏል።
አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት ግለሰቦቹ ነገ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብሏል ፓሊስ።
የኢትዮጵያ አየርመንገድ በነሐሴ 16፣2016 ባወጣው መግለጫ ስለመቀሌው በረራ በቀጥታ ባይጠቅስም በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ለበረራ መሰረዝ ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል።
መግለጫው "ዛሬ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከለሊቱ 09፡00 ሰአት ጀምሮ በነበረው ከፍተኛ ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንያት አብዛኞቹ ወደ አዲስ አበባ ሲያቀኑ የነበሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሊያርፉ ባለመቻላቸው በአቅራቢያ ወደሚገኙ አማራጭ ኤርፖርቶች ተመልሰው እንዲያርፉ ተገደዋል"ብሏል።