ኤምሬትስ ሩሲያና ዩክሬን የእስረኞች ልውውጥ ስምምነት እንዲደርሱ ስታደርግ የዛሬው ለሰባተኛ ጊዜ ነው ተብሏል
ሩሲያ እና ዩክሬን በዛሬው እለት የጦር ምርኮኞችን ተለዋውጠዋል።
በአረብ ኤምሬትስ አደራዳሪነት ከስምምነት በተደረሰው የእስረኞች ልውውጥ ሁለቱ ሀገራት እኩል 115 እስረኞችን ተለዋውጠዋል ብሏል አናዶሉ በዘገባው።
ዩክሬን ከ18 ቀናት በፊት በምዕራባዊ ሩሲያ ኩርስክ ክልል ጥቃት ከከፈተች በኋላ ከሞስኮ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የእስረኞች ልውውጥ ያደረገችው።
ሩሲያ የለቀቀቻቸው የዩክሬን ወታደሮች የሀገራቸውን ብሄራዊ መዝሙር ሲዘምሩ ታይተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የተለቀቁት የጦር እስረኞች በባህር ሃይል እና በእግረኛው ጦር በድንበር አካባቢ ተሰማርተው ግዳጃቸውን ሲወጡ የቆዩ ጀግኖች ናቸው ብለዋል።
ዛሬ ከተለቀቁት 115 እስረኞች ውስጥ 82ቱ በ2022 የማሪዮፖል ወደብ በሩሲያ እንዳይያዝ መታገላቸውን የኬቭ ባለስልጣናት መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ዛሬ በጦር እስረኞች ልውውጡ የተለቀቁት የሩሲያ ወታደሮች በኩርስክ ክልል ሲካሄድ በቆየው ውጊያ የተያዙ መሆናቸውን ገልጿል።
ሁሉም (115) የሩሲያ ወታደሮች በአሁኑ ወቅት በቤላሩስ እንደሚገኙና ህክምና ተደርጎላቸው ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
ሩሲያ እና ዩክሬን ከየካቲት 2022 ወዲህ 55 ጊዜ የጦር እስረኞች ልውውጦችን አድርገዋል።
ከዛሬው የእስረኞች ልውውጥ በፊትም በሃምሌ ወር 95 ምርኮኞችን መለዋወጣቸው የሚታወስ ነው።
አረብ ኤምሬትስም ሁለቱ ሀገራት የገቡበትን ጦርነት በንግግር እንዲቋጩት ጥረት ከማድረግ ባሻገር የእስረኞች ልውውጦች እንዲያደርጉ ስታሸማግል ቆይታለች።
በዛሬው እለት የተካሄደው የጦር እስረኞች ልውውጥም በኤምሬትስ አሸማጋይነት የተካሄደ ሰባተኛው የምርኮኞች ልውውጥ ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪም የአቡዳቢን ጥረት በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ አወድሰዋል።