ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ ከደገፉት ውስጥ 54 በመቶዎቹ በውሳኔያቸው ተጸጽተዋል ተባለ
ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት መውጣቷን ተከትሎ 100 ቢሊዮን እንደምታጣ ተገልጿል
ብሪታንያ በህዝበ ውሳኔ በ2016 ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት መወሰኗ ይታወሳል
ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ ከደገፉት ውስጥ 54 በመቶዎቹ በውሳኔያቸው ተጸጽተዋል ተባለ፡፡
በፈረንጆቹ 2016 ላይ በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ለመውጣት መወሰኗ አይዘነጋም፡፡
ሰታቲስቲካ የተሰኘው የብሪታንያው የጥናት ተቋም ባወጣው ጥናት መሰረት አሁን ላይ ሀገራቸው ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ ድምጽ ከሰጡ ዜጎች ውስጥ 54 በመቶዎቹ በውሳኔያቸው እንደሚጸጸቱ አስነብቧል፡፡
34 በመቶዎቹ ደግሞ አሁንም ውሳኔያቸው ትክክል መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ሀገራቸው ከአውሮፓ ህብረት ከተነጠለች በኋላ በብዙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች ያሰበችውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆነች ግን ጠቅሰዋል ተብሏል፡፡
ከአውሮፓ ህብረት የመውጣቱ የሕዝበ ውሳኔ ሰኔ 2016 ላይ የተካሄደ ሲሆን 51 ነጥብ 9 በመቶ ብሪታንያዊያን ከህብረቱ ለመነጠል ድምጽ ሰጥተው ነበር፡፡
የህዝበ ውሳኔውን ተከትሎም የወቅቱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዴቪድ ካሜሩን ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው አይዘነጋም፡፡
ብሪታንያ ከህብረቱ መውጣቷን ተከትሎ ከ3 ሺህ በላይ ሚሊየነሮች ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና እስያ ተሰደዋል ተብሏል፡፡
እንዲሁም እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስም ብሪታንያ ከህብረቱ በመውጣቷ ምክንያት የ100 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚደርስባትም ከዚህ በፊት ተጠቅሷል፡፡