ስኮትላንድ ሁለተኛውን ህዝበ ውሳኔ አድርጋ ከብሪታንያ ለመነጠል እየተንቀሳቀሰች ነው
የብሪታንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ለስኮትላንድ የመነጠል ህዝብ ውሳኔ ፍቃድ አልሰጥም ብሏል
መነጠልን የሚያቀነቅነው የስኮትላንድ ብሄራዊ ፓርቲ በበኩሉ ረቂቅ የህዝበ ውሳኔው ማስፈጸሚያ ሰነዱን ለማጽደቅ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቷል
ስኮትላንድ በህዝበ ውሳኔ ከብሪታንያ ለመነጠል የምታደርገው ጥረቷ መቀጠሉ ተነግሯል።
የስኮትላንድ ራስ ገዝ መንግስት መሪዋ ወይም ቀዳሚት ሚኒስትር ኒኮላ ስተርጂን በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት የስኮትላንድ ብሄራዊ ፓርቲ (ኤስ ኤን ፒ) በመጪው መጋቢት ፣ 2022 አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ያደርጋል።
በዚህ ጉባኤም ፓርቲው የብሪታንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ መገዳደር የሚችል አቋም ይዞ ይወጣል ብለዋል የአፍቃሬ ስኮትላንድ ፓርቲ መሪዋ ኒኮላ ስተርጂን።
የስኮትላንድ ራስ ገዝ መንግስት በቀጣዩ አመት ጥቅምት ወር ሁለተኛውን ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ በብሪታንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በህዳር ወር 2022 ውድቅ ተደርጓል።
ስኮትላንድ የብሪታንያ ምክር ቤት ሳያጸድቀው ነጻ ሀገር መሆን የሚያስችላትን ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ ውሳኔ ማሳለፍም ሆነ ምርጫውን ማካሄድ አትችልም ነው የሚለው ውሳኔው።
የኒኮላ ስተርጂን አስተዳደር ግን የስኮትላንድ ብሄራዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተረቀቀው የህዝበ ውሳኔ ሰነድ ላይ አስቸኳይ ምክክር አደርጎ እንዲያጸድቀው መጠየቃቸው ተገልጿል።
የብሪታንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስኮትላንድን ነጻ ሀገር የመሆን ፍላጎት መገደቡን ቀጥሏል፤ እናም በራሳችን መንገድ ሄደን ከብሪታንያ እንነጠላለን የሚሉ የኤዲንበርግ ፖለቲከኞች ቁጥር እየተበራከተ ነው።
ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላም የስኮትላንድን ከብሪታንያ መነጠል የሚደግፉት ቁጥር መጨመሩን የህዝብ አስተያየትን የሚሰበስበው ሬድፊልድ ኤንድ ዊልተን የተባለ ተቋም ገልጿል።
ድምጻቸውን ከሰጡ ስኮትላንዳውያን ውስጥ 49 ከመቶው ህዝበ ውሳኔው በፍጥነት ከተደረገ ከብሪታንያ መነጠሉን እንደሚደግፉ ተናግረዋል። 45 ከመቶው ደግሞ መነጠሉን አንደግፈውም ማለታቸው ተጠቁሟል።
ለ300 አመታት የብሪታንያ አካል ሆና የቆየችው ስኮትላንድ በ2014 ባደረገችው ህዝበ ውሳኔ 55 በመቶ የሚሆነው ስኮትላንዳዊ አንድነትን ሲመርጥ የመነጠል ሃሳቡ የተዳፈነ መስሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ብሪታንያ በ2016 ከአውሮፓ ህብረት ስትወጣ ውሳኔው ክፉኛ እንደሚጎዳቸው የገለጹ ስኮትላንዳውያን ዳግም የመነጠል ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ መወትወት ጀምረዋል።