ሩዋንዳ የአየር ክልሌን ጥሷል ባለችው የኮንጎ ወታደራዊ ጄት ላይ ተኮሰች
ኪንሻሳ ግን “የሩዋንዳን የአየር ክልል አልጣስኩም፤ ግልጽ የጦርነት አዋጅ ነው” ብላዋለች
ሁለቱ ሀገራት ኤም23 ከተሰኘው ታጣቂ ቡድን ጋር በተያያዘ ግንኙነታቸው ሻክሯል
ሩዋንዳ የአየር ክልሌን ጥሶ ገብቷል ያለችውን የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወታደራዊ አውሮፕላን ለመምታት ተኩስ መክፈቷ ተነገረ።
አውሮፕላኑ ከተከፈተበት ተኩስ ማምለጡን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም በኮንጎ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተዘዋወሩ ነው።
ኪንሻሳ ግን የሩዋንዳን አየር ክልል ጥሳ አለመግባቷንና የኪጋሊ እርምጃ ግልጽ ጸብ ፍለጋ ነው ብላዋለች።
ወታደራዊ አውሮፕላኑ የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት ጎማ በተሰኘችው ከተማ ማረፉንም ነው ባወጣችው መግለጫ ያስታወቀችው።
“በኮንጎ የአየር ክልል ውስጥ እየበረረ የነበረውን አውሮፕላን ለመምታት መሞከር የጦርነት አዋጅ ነው” በሚልም ተቃውሟዋን ገልጻለች።
ሩዋንዳ ከዚህ ቀደምም የአየር ክልሌን ጥሶ ገብቷል ባለችው የኮንጎ አውሮፕላን ላይ መሰል እርምጃ መውሰዷን ሮይተርስ አስታውሷል።
በምክንያትነት የምታቀርበውም “ራስን የመከላከል እርምጃ” ነው የሚል ነው።
የሀገሪቱ መንግስት ቃልአቀባይ ዮላንዴ ማኮሎም “ሩዋንዳ የዴሞክራሲያዊ ሬፐብሊክ ኮንጎ መንግስትን ከወረራው እንዲታቀብ ጠይቃለች” ማለታቸው ነው በዘገባው የተጠቀሰው።
ኮንጎ፣ የመንግስታቱ ድርጅት እና ምዕራባውያን ሀገራት ሩዋንዳን በምስራቃዊ ኮንጎ የሚገኙ የኤም23 ታጣቂዎች ትደግፋለች በሚል ይወቅሷታል።
ኪጋሊ ግን በርካታ ከተሞችን የተቆጣጠረውን ታጣቂ ቡድን እንደማታስታጥቅ ነው የምትገልጸው።
የቀጠናው ሀገራት መሪዎች ሀገራቱን ለማቀራረብ በህዳር ወር 2022 ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ቢያደርጉም አሁንም መካሰሱ ቀጥሏል።
የዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሴክዴ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፥ 450 ሺህ ዜጎችን ያፈናቀሉ ታጣቂዎች በስምምነቱ መሰረት አካባቢዎቹን ለቀው አልወጡም ብለዋል።
ኪንሻሳ እና ኪጋሊ በኤም23 ታጣቂዎች ምክንያት የገቡበት ፍጥጫ በትናንቱ የአውሮፕላን መምታት ሙከራ ይበልጥ እንዳይባባስ ተሰግቷል።