በዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፈው ኳታር ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት ምን ይመስላል?
ኳታር ከ200 ቢሊየን ዶላር ወጪ ያደረገችበት የዓለም ዋንጫ መሰናዶ በውጤት ይታጀብ ዘንድ ዜጎቿ ይጠብቃሉ
ኳታር የምታስተናግደው የ2022 የአለም ዋንጫ ሊጀመር 10 ቀናት ብቻ ቀርውታል
የባህረ ሰላጤዋ ሀገር ኳታር ቢሊየን ዶላሮችን ያወጣችበትን መሰናዶ ለአለም ማሳየት ልትጀምር 10 ቀናት ቀርተዋል።
ኳታር በምድብ 1 ከኢኳዶር፣ ሴኔጋልና ኔዘርላንድስ ጋር ተመድባለች።
መስከረም ወር ላይ ሊጓን አቋርጣ ልምምድ የጀመረችው ኳታር ከኢኳዶር በምታደርገው ጨዋታ የ2022 የአለም እግር ኳስ ዋንጫ ይጀመራል።
ከ200 ቢሊየን ዶላር ወጪ ያደረገችበት መሰናዶ በውጤት ይታጀብ ዘንድ ዜጎቿ ይጠብቃሉ።
ኳታር እና የአለም ዋንጫ
በፈረንጆቹ 1971 ነፃነቷን ያወጀችው ኳታር የአለም ዋንጫ ተሳትፎ የላትም። ራሷ ያዘጋጀችው ከቀናት በኋላ የሚጀመረው የአለም ዋንጫ የመጀመሪያዋ ሆኖ ይከተባል።
በ1990ው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ በሳዑዲ አረቢያ ተሸንፋ ከምድቧ 3ኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ውጤት ከጫፍ ደርሳ የተመለሰችበት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
በ1960 የእግር ኳስ ማህበር መስርታ ከሶስት ዓመት በኋላ የአለም አቀፉ እግርኳስ ማህበር (ፊፋ) አባል ብትሆንም በአለም አቀፍ መድረክ ውጤታማ አልሆነችም።
60 ሺህ ተመልካቾችን የሚይዘው፤ ጣሪያው ተከፍቶ የሚዘጋው የአል ባይት ስታዲየም ይህን ታሪክ ለመቀየር ዝግጁ ሆኗል፤ ኳታር የመጀመሪያውን የአለም አቀፍ ጨዋታዋን ከኢኳዶር ጋር ታደርጋለች።
ስፔናዊው የኳታር ኳስ አዋቂ
በፈረንጆቹ 2006 ወደ ኳታር የዘለቁት ፍሌክስ ሳንቼዝ የኤሚሮቹ ፍቅር አጥብቆ ይዟቸዋል። የዶሃ ቆይታቸው ዘለግ ማለት የኳታርን እግር ኳስ እንደ ሳንቼዝ የሚረዳ የለም እስከሚባል ድረስ ጠቅሟቸዋል ነው የሚባለው።
ስፔናዊው አሰልጣኝ በወጣቶቾ አካዳሚ ላይ ሰርተው በ2017 ብሄራዊ ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ ሲሰጣቸው ግን የተጠበቀውን ውጤት አላመጡም፤ ለ2018ቱ የዓለም ዋንጫም አላሳለፏትም።
ኳታር የ2019 የእስያ ዋንጫን እንድታነሳ ያደረጉት ሳንቼዝ፥ በዚሁ አመት በተደረገው የኮፓ አሜሪካ ግጥሚያ ያሳዩት አቋምም ተስፋ እንዲጣልባቸው አድርጓል።
የኳታር ብሄራዊ ቡድን
"ነብዮቹ" ወይም አናቢዎቹ የኳታር ብሄራዊ ቡድን መጠሪያ ተቀፅላ መጠሪያ ነው።
ብሄራዊ ቡድኑ ከካናዳ፣ ከቺሊ፣ ጓቲማላ እና ሌሎች ሀገራት ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርጓል። አሰልጣኝ ሳንቼዝ ከዝግጅት ጋር የተያያዘ ሰበብ እንዳይደረድሩ በቂ በጀት ተመድቦ ወዳሻቸው እንዲጓዙ ሆኗል።
ነብዮቹ ያስመዘገቡት ውጤት ግን የአዘጋጇን ሀገር ቅርብ ወራጅነት ያሳያል ነው የተባለው፤ ከቺሊ ጋር 2 ለ 2 ከተለያዩበት ጨዋታ ውጭ የትንሿን ሀገር ተስፋ የሚያሳድግ ውጤት አልታየም።
ቡድኑ ከቀናት በኋላ ለሚጀመረው ግጥሚያ በስፔኗ ማርቤላ ከተማ አድፍጦ ዝግጅት ላይ ነው።
የስፔኑ ዲያሪዬ አስ ጋዜጣም ሰለዚሁ ጉዳይ ሲጠቅስ፥ "ሊቨርፑል በ2019 ለሻምፒዬንስ ፍፃሜ ደርሶ በነበረበት ወቅት ራሱን ሰውሮ እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት እንኳን ተጫዋቾቹ በብስክሌት ሲንቀሳቀሱ እናይ ነበር፤ የኳታር ግን ከዚህ የከፋ ነው" ብሏል።
ተጠባቂው የኳታር ኮከብ - ኤክራም አፊፊ
እንደ ኤሌክትሪክ ፈጣን አጥቂ ነው፤ ቀጣዩ የእስያ ፈረጥ በአለም ዋንጫው ነጥሮ ይወጣል የሚሉ አስተያየቶች ከዘደ ዶሃ እየወጡ ነው።
በኳታር ሱፐር ሊግ ከሁለት አመት በፊት ክለቡ አል ሳድ ዋንጫ ሲያነሳ አፊፊ ልዩ ተሰጥአ እንዳለው አሳይቷል። የወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ ዣቪ ሄርናንዴዝም "የሚገርም ብቃት እንዳለው ደጋግሜ ነግሬዋለው" ሲል ተደምጧል።
ከጉዳት የተመለሰው አፊፊ የኳታር የፊት መስመርን ይመራል። ብዙ ያልተዘመረለትና አል ዱሄየል ለተሰኘው ቡድን የሚጫወተው ባሳም አል ራዊም የኋላ ደጀን ሆኖ ሀገሩን ከጥቃት ይጠብቃል።
ሳድ አል ሼብም የሀገሩን የግብ መረብ ላለማስደፈር ይታገላል ተብሎ ይጠበቃል። ዶሃ በአለም አቀፍ ደረጃ በትልልቅ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሏትም።
በወጣቶች አካዳሚ የጀመረቻቸው ስራዎች ግን ተስፋ ሰጪ ናቸው። ከአለም 50ኛ ላይ የተቀመጠችው ኳታር በብዙ የደከመችበትን የአለም ዋንጫ በድል ትጀምረው ይሆን? 10 ቀናትን መጠበቅ ከመልሱ ያደርሰናል።