የኃይል አቅርቦት የተቋረጠባቸው ከተሞች ዳግም ኃይል ማግኘት መጀመራቸውን ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ
ኤሌክትሪክ ኃይል ሸዋሮቢት አካባቢ የተበጠሰውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የመጠገን ስራ አልተጠናቀቀም ብሏል
ኤሌክትሪክ ኃይል በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መበጠስ ምክንያት በአማራ፣ በትግራይ አና በአፋር ክልል ያሉ ከተሞች ኃይል እንደተቋረጠባቸው ያስታወቀው ከትናንት በስትያ ነበር
የኃይል አቅርቦት የተቋረጠባቸው ከተሞች ዳግም ኃይል ማግኘት መጀመራቸውን ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በኃይል ማስተላላፊያ መስመሮች ላይ በደረሰው የመበጠስ አደጋ የኃይል አቅርቦት የተቋረጠባቸው ከተሞች ድጋሚ ኃይል ማግኘት መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ትናንት ምሽት አስታውቋል።
ኤሌክትሪክ ኃይል በአማራ ክልል ውስጥ ባሉ በሁለት ቦታዎች ላይ በደረሰው የማስተላለፊያ መስመሮች መበጠስ ምክንያት በአማራ፣ በትግራይ አና በከፋር ክልል ያሉ ከተሞች ኃይል እንደተቋረጠባቸው ያስታወቀው ከትናንት በስትያ ነበር።
የማስተላለፊያ መስመሮቹ የተበጠሱት በሰሜን ወሎ ዞን ጋሸና እና በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት አቅራቢያ መሆኑን ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጾ ነበር።
ኤሌክትሪክ ኃይል ትናንት ባወጣው መግለጫው እንዳስታወቀው ጋሸና ላይ የተበጠሰው ከባህርዳር -ጋሸና-አላማጣ የተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል መስመር ተጠግኖ ወደ አገልግሎት ገብቷል።
የኃይል መስመሩን መጠገን ተከትሎ በአማራ ክልል፣ ክልሉን ዋና ከተማ ባህርዳር፣ ጎንደር እና ሌሎች ከተሞች ኃይል ሲያገኙ በትግራይም የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ በርካታ ከሞች ዳግም ኃይል አግኝተዋል ብሏል ኤሌክትሪክ ኃይል።
ኤሌክትሪክ ኃይል ሸዋሮቢት አካባቢ የተበጠሰውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የመጠገን ስራ አልተጠናቀቀም ብሏል።
ከሽዋሮቢት-ከምቦልቻ በተዘረጋው መስመር ኃይል ሲያገኙ የነበሩት ወልዲያ እና ከምቦልቻ እንዲሁም የአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራና ሌሎች ከተሞች ድጋሚ ኃይል እንዲያገኙ የጥገና ስራ በመሰራት ላይ መሆኑን ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጿል።