ዩክሬን ሩሲያን በአጭር ጊዜ ድል ማድረግ እንደማትችል የአሜሪካ ጦር ዋና አዛዥ ገለጹ
አሜሪካ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል አዛዡ ተናግረዋል
በዩክሬን ግዛት ውስጥ ያለው የሩሲያ ጦር አሁንም ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ ተገልጿል
ዩክሬን ሩሲያን በአጭር ጊዜ ድል ማድረግ እንደማትችል የአሜሪካ ጦር ዋና አዛዥ ገለጹ።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ዘጠኝ ወራት ያስቆጠረ ሲሆን ይህ ጦርነት በዓለም ምግብ፣ ነዳጅ እና ዲፕሎማሲ ላይ ጉዳቶችን እያደረሰ ይገኛል።
ዩክሬን በሩሲያ ላይ ድል እንድትቀዳጅ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ናቸው።
ሩሲያን ከዓለም ንግድ እና ዲፕሎማሲ የሚነጥሉ እርምጃዎችን ከመውሰድ ጀምሮ ለዩክሬን የቀጥታ ጦር መሳሪያ ድጋፍ እየተደረገላትም ይገኛል።
በዚህም መሰረት ዩክሬን በሩሲያ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን መልሳ በመቆጣጠር ላይ ትገኛለች።
የአሜሪካ ጦር አዛዥ ማርክ ሚሊ እንዳሉት ዩክሬን በራሷ እና በምዕራባዊያን ሀገራት ድጋፍ በሩሲያ ላይ ድል እየተቀዳጀች መሆኑን ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሞስኮ በህዝበ ውሳኔ ወደ ራሷ የጠቀለለቻት ኬርሰን ግዛት በዩክሬን ጦር መያዟን ተከትሎ በርካቶች ዩክሬን ድል እየቀናት እንደሆነ ቢናጉሩም የሩሲያ ጦር አቅም አሁንም ከፍተኛ መሆኑን እና ዳግም ጥቃት ሊከፍት እንደሚችልም አዛዡ ጠቁመዋል።
ይሁንና ዩክሬን በሩሲያ ላይ ድል መቀዳጀቷ አይቀርም የሚሉት አዛዡ ይህ ድል ግን በቅርቡ ሊሆን አይችልም ሲሉም አክለዋል።
ዩክሬን ከሩሲያ እየደረሰባት ያለውን ጥቃት ለመመከት አሜሪካ የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ተያያዥ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል አዛዡ ገልጸዋል።
የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ዋና ጸሀፊ ጀንስ ስቶልትንስበርግ ዩክሬን ከሩሲያ ጦር ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ማስለቀቋን ተከትሎ የሩሲያ ጦር አቅምን አሳንሶ ማየት ስህተት መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
አሜሪካ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለዩክሬን ከ19 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎች መለገሷ ይታወሳል።